ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትሱ የብረታ ብረት ኩባንያ - ‘ዩኤስ ስቲል’ ያለበትን ዕዳ በሙሉ ክፍያ በመፈጸም፤ በ14.9 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ወደ ጃፓኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ‘ኒፖን ስቲል’ ለማዛወር የተያዘውን ዕቅድ እንደሚያግዱ አስታወቁ።
ትራምፕ በትላንትናው ዕለት ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት መላላኪያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ በአንድ ወቅት “ገናና እና ብርቱ የነበረው ‘ዩኤስ ስቲል’” የውጭ አገር ኩባንያ በሆነው በጃፓኑ ‘ኒፖን ስቲል’ የመገዛቱን ዕድል ሙሉ በሙሉ እቃወማለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።
አያይዘውውም "በተከታታይ የሚፈጸሙ የግብር ማበረታቻዎችን እና ቀረጥ ነክ ርምጃዎችን በመውሰድ ‘ዩኤስ ስቲል ዳግም ገናና እና ጠንካራነቱን እንዲጎናጸፍ እናደርገዋለን’ ያሉት ትራምፕ፤ ‘ይህም በፍጥነት እውን ይደረጋል፣ እንደ ፕሬዝዳንትም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን አደርጋለሁ" ሲሉ አቁማቸውን ገልጸዋል።
ከኒፖን ስቲል ጋራ የደረሰው የሽያጭ ስምምነት ‘ሞን ቫሊ ፔንስልቬንያ’ በሚገኘው ፋብሪካው ላይ በቂ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ያስችለኛል’ ሲል የተከራከረው ‘ዩኤስ ስቲል’ በበኩሉ “ሽያጩ ከታገደ ግን ፋብሪካውን ለመዝጋት እገደዳለሁ” ብሏል።
ገዥው ‘ኒፖን ስቲል’ በፊናው ከትራምፕ አስተያየት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ “የዩናይትድ ስቴትስን ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ የሀገር ውስጥ የአቅርቦት ስርአቷን ፈታኝ ሁኔታዎችን የመቋቋም አቅም እና የአሜሪካን ብሄራዊ ደህንነት በሚያጠናክር መልኩ ዩኤስ ስቲል’ን ተንከባክቦ ለመያዝ እና ለማሳደግ ቁርጠኝስ ነኝ” ብሏል።
“በማኅበር የተደራጁ ሠራተኞች ባሉት ‘ዩኤስ ስቲል’ ኩባንያ ላይ ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ መዋዕለ ንዋይ ወጭ እናደርጋለን። ዓንምለም አቀፍ ደረጃው የተጠበቀ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅማችንን ተጠቅመንም በዩኤስ ስቲል ውስጥ የሚገኙ አሜሪካውያን የብረታብረት ሰራተኞች ለአሜሪካውያን ደንበኞቻቸው ጥራታቸው እጅግ የላቀ የብረታ ብረት ምርቶችን እንዲያመርቱ እናስችላቸዋለን" ሲል የጃፓኑ ኩባንያ እቅዱን ዘርዝሯል።
የሽያጭ ስምምነቱን ተከትሎም የባለቤትነት ይዞታ ዝውውሩ የያዝነው የአውሮፓውያኑ 2024 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሥልጣን ላይ እያሉ ይጠናቀቃል’ ሲል ‘ኒፖን ስቲል’ ባለፈው ወር በተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ምርጫ ማግስት ነበር ይህንኑ እቅዱን ይፋ ያደረገው።
ይሁን እንጂ ባይደንም ’ዩኤስ ስቲል’ “በአገር ውስጥ ኩባንያ ባለቤትነት የሚተዳደር፣ የአሜሪካ ብረታ-ብረት ኩባንያ ሆኖ መቀጠሉ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ስምምነቱን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የትራምፕ በዓለ ሲመት እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ጥር 20 ይፈጸማል።
መድረክ / ፎረም