የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከኢራን ጋራ የኑክሌር ድርድር ማድረግ እንደሚሹ ለሀገሪቱ መሪዎች ትላንት ሐሙስ ደብዳቤ መላካቸውን አስታውቀዋል።
የኢራን መሪዎች ለመነጋገር ይስማማሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ትረምፕ አስታውቀዋል።
ትረምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ኢራን ለድርድር ትቀርባለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉና፣ ይህም ለኢራን መልካም ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።
“ደብዳቤውን ለማግኘት የፈለጉ ይመስለኛል፣ ሌላው አማራጭ ግን አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክኒያቱም የኑክሌር መሣሪያ እንዲኖራቸው መፍቀድ አይቻልም “ ብለዋል ትረምፕ፡፡
ደብዳቤው የተላከው ለኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ኻሚኒ እንደሆነ የተገመተ ሲሆን፣ ይህንኑ ከኋይት ሃውስ ለማጣራት የተደረገው ሙከራ መልስ ባለመገኘቱ እንዳልተሳካ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
የሩሲያው ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ርያብኮቭ የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም አስመልክቶ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት በተመለከተ ከኢራኑ አምባሳደር ካዜም ጃላሊ ጋራ እንደተወያዩ የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ዓርብ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም