በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትረምፕና የማክሮን ኅብረት ይሰምር ይሆን?


የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመጭው ሣምንት ከሰኞ እስከ ረቡዕ ዋሺንግተን ዲሲ ናቸው። ከአሜሪካ አቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው ንግግሮች ፍሬ ያስገኙ ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

መስዮ ማክሮን ሚስተር ትረምፕን ሊያነጋግሩ ወደ ዋሺንግተን የሚበርሩት አትላንቲክ አቋራጩ ውጥረት በርከት ባሉ ጉዳዮች ላይ በከረረበት እና ግለቱ ባየለበት ወቅት ቢሆንም ይህ ጉዞ ግን ሁለቱ መሪዎች ለብዙዎች በማይታመን ሁኔታ ግንኙነቶቻቸውን ጠበቅበቅ ስለማድረጋቸው ዋቢ እንደቆመ እየተነገረ ነው።

ማክሮን የትረምፕ እንግዳ የሚሆኑት ከነሙሉ አጀብና ቦርሣ ሙሉ ጉዳዮቻቸው ነው። ለሦስት ቀናት በኦፊሴል አሜሪካ ይቆያሉ።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ፓሪስ ሄደው በነበረ ጊዜ ወታደራዊ ሰልፍ በፊታቸው ሲያልፍ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ፓሪስ ሄደው በነበረ ጊዜ ወታደራዊ ሰልፍ በፊታቸው ሲያልፍ

ፈረንሣይ የዛሬ 229 ዓመት በታዋቂው አብዮቷ ዘመን ባስቲይ ግምብ የተወረረበትና የተያዘበትን ብሔራዊ ክብረ በዓሏን፤ ላ ፌት ናሲዮናልን ባለፈው ሐምሌ ስታከብር ዶናልድ ትረምፕ ከአውሮፓዊያኑ የአሜሪካ ወዳጆች ጋር ሊታደሙ ፓሪስ የተገኙ ጊዜ ኢማኑኤል ማክሮን ልዩ መስተንግዶ አድርገውላቸው ነበር። ርችቱ ነሽ... መድፉ ነሽ... ወታደራዊ ማርሽና ሰልፉ ነሽ... መንግሥታዊ እራቱ ነሽ... ምኑ ቅጡ እንዲሉ... ምኑ ቀረ? በዓሉ - ሎ ካቶርዝ ዡዬ - ሐምሌ ሰባት /በኢትዮጵያ ጊዜ መስፈሪያ ሲመነዘር ማለት ነው/ የሚገባው ክብር ሁሉ ለሚስተር ትረምፕም ተደርጓል። አሁን የዚያ የቀይ ምንጣፍ አቀባበል ባለ ሣምንት የአሜሪካው መሪ ናቸው።

በርግጥ ያኔ ፓሪስ ላይ እራት የተበላው እጅግ ድንቅ በተባለ ቱር ኤፌል - ታላቁ አይፍል ማማ ዘንድ በሚገኝ የተቀናጣ ሆቴል ነበር። ሚስተር ትረምፕ ደግሞ ለአሜሪካ በባለ እጅግ ብዙ እሴቱ - “ተመን የለሽ” እንዲሉም እጅግ ታሪካዊ በሆነ ሥፍራ ነው ለማክሮን ግብር ሊጥሉ እያስደገሱ ያሉት - የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ፈጣሪ አባት “Father of the Nation” ተብለው የሚታወቁት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቷ የጆርጅ ዋሺንግተን መኖሪያ ቤት ... ገናናው ማውንት ቨርነን

ለመስዮ ማክሮን መድፍ ይተኮስላቸዋል - ሃያ አንድ ጊዜ! እተወካዮች ምክር ቤቱም ተገኝተው ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ዲስኩር ይሰጣሉ።

ይሄ ሁሉ ታዲያ የመስተንግዶ ሽብርቅርቅና ሽር ጉድ ነው እንጂ ጠጠር ያሉ ቁም ነገሮች፣ እሰጥ አገባና የ “እውነት እውነቱን እንነጋገር” መራራ ምልልሶች አይቀሬ እንደሆኑም እየተሰማ ነው። ይህንን እንግዳም ተቀባይም ያውቁታል...

ኢራን፣ ንግድ፣ ኢየሩሳሌም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ... ፕሬዚዳንት ትረምፕ እና ፕሬዚዳንት ማክሮን ዐይን ለዐይን፤ ብረት ለብረቱ የማይተያዩባቸው ጉዳዮች ዝርዝር እንዲህ አጭር አይመስልም።

“ሚስተር ትረምፕ ባለፈው ዓመት ወደ ፓሪስ የመጡ ጊዜ ነገሩ የግንኙነቶቹ መጀመር ፈንጠዝያ ነበር ... አሁን ሥራ መሥራት አለባቸው፤ ያ ሥራ ደግሞ እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው” - ፊሊፕ ሞሮ ዴፋርገስ የፈረንሣይ ዲፕሎማት ነበሩ፤ የአውሮፓ ጉዳዮች አዋቂም ናቸው ይህንን ያሉት።

ኢራን፣ ንግድ፣ ኢየሩሳሌም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ... ፕሬዚዳንት ትረምፕ እና ፕሬዚዳንት ማክሮን ዐይን ለዐይን፤ ብረት ለብረቱ የማይተያዩባቸው ጉዳዮች ዝርዝር እንዲህ አጭር አይመስልም።

ባለፈው ታኅሣስ ፓሪስ ፕላኔት ሳሚት (Planet Summit) የተባለውን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተነጋገረ የዓለም መሪዎች ጉባዔ - 'የምድር ስብሰባ'ን ያስተናገደች ጊዜ ፕሬዚዳንት ትረምፕ አልተጋበዙም ነበር። ሃገራቸው ከፓሪሱ የአየር ንብረት ውል እንድትወጣ መወሰናቸው ብዙዎችን አስቆጥቷል፤ ብዙዎችን አስኮርፏል ... በቀጥታም በአሽሙሩም ትረምፕ ላይ የቁጣ ውርጂብኝ ካዘነቡባቸው መሪዎችና የተፈጥሮ አካባቢ ደኅንነት ተሟጋቾች መሃል ማክሮን ስለመገኘታቸው እማኝ አይቆጠርም።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን - ፓሪስ፣ ፈረንሣይ - ሐምሌ 6/2009 ዓ.ም.
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን - ፓሪስ፣ ፈረንሣይ - ሐምሌ 6/2009 ዓ.ም.

ዛሬ ግን ትረምፕ ወደ አውሮፓ ፊታቸውን ዘወር አድርገው 'ማንን ልጣራ' ያሉ እንደሆነ የሚጀምሩት ከኢማኑኤል ማክሮን ነው። ማክሮን እኮ የፕሬዚዳንት ትረምፕን ሃሣብና እስትንፋስ ለሌላ የአውሮፓ መሪዎች በሚገባቸው ቋንቋ፣ በሚገቧቸው ምልክቶች ሊያተረጉሙላቸው የሚችሉ ሰው ናቸው ... በዚያ ላይ ደግሞ ለአውሮፓ ጉዳዮችም ግንባራቸውን ሰጥተው የሚሰለፉ ...

የጀርመን ማርሻል ፈንድ የሚባለው በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ መካከል መተባበርን ለማጠናከር የሚሠራው ወገናዊ ያልሆኑ የሃሣብ አብላዮች ጠቢባን አሜሪካዊ የሕዝብ ፖሊሲ ቡድን የፓሪስ ቢሮ ዳይሬክተር አሌክሳንድራ ዴ ሁፕ ሼፈርና ሌሎችም የእርሣቸው ቢጤ ባልደረቦቻቸውና ተንታኞች እያሰቡበት ያሉት ጉዳይ አለ፤ የዋሺንግተን ጉዞ እንዲህ ዓይነቱ የሲሦ ሚዛን ስለመሥራቱ ዋና መፈተሻ ነው የሚሆነው “ከዋሺንግተን ጋር በተለይ ደግሞ ከትረምፕ ጋር አብዝተው የቆሙ ካስመሰለባቸው፤ በተለይ ደግሞ የፈረንሣይና የአውሮፓ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ትረምፕ ሊወስዷቸው በሚችሉ ውሣኔዎች ምክንያት አደጋ ላይ የሚወድቁ ከሆነ እቤታቸው ፈረንሣይ ውስጥ ብዙ ችግር ይጠብቃቸዋል” ብለዋል።

ፈረንሣይ እስከዛሬ ከነበሯት ፕሬዚዳንቶች ሁሉ እጅግ ወጣቱና አሜሪካ ከነበሯት ፕሬዚዳንቶች ሁሉ እጅግ አዛውንቱ የሚፈጥሩት ኅብረት ለአንዳንዶች የሚደንቅ፤ የማይመስል ነገር ሆኗል። ማክሮን በዘርፈ-ብዙና ወገነ-ብዙ ተቋማትና ትብብሮች የሚያምኑ መሪ ናቸው፤ ትረምፕ የሚሉት “አሜሪካ ትቅደም” ነው። ማክሮን አብዝተው ሠራተኛ የሥራ ሱሰኛ ናቸው -- ትረምፕ አብዝተው ትዊተኛ - የትዊት ሱሰኛ ናቸው - ይሏቸዋል ስለሁለቱም በንፅፅር ሲናገሩ።

አሌክሳንድራ ዴ ሁፕ ሼፈር የሚያዩት ደግሞ ሌላ ጥግ አለ... “ፈረንሣይና ዩናይትድ ስቴትስ የሚያቆራኛቸው፤ ደግሞም ጀርመንና እንግሊዝ ለዋሺንግተን ሊሸጡ የማይችሉት ነገር - ወታደራዊ ትብብር የሚባለው ነው። ይህ የጄነራልና የጄነራል ግንኙነት ጉዳይ ነው።”

እንዲህ ዓይነቱ ትብብር በአፍሪካው ሳህል አውራጃ ውስጥ ከፅንፈኛ ቡድኖች ጋር በተደረጉ ፍልሚያዎች ታይቷል፤ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ምርምር፣ ማምረቻና ማከማቻ ነበሩ የተባሉ የሦሪያ ተቋማት ባለፈው ሣምንት የተደበደቡ ጊዜ ታይቷል። ትረምፕ ወታደሮቻቸውን ከሦሪያ እንደሚያወጡ ሲናገሩ ማክሮን ሦሪያ ውስጥ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትኄ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ጊዜ፣ ጥሪትና ሃሣብ ለማፍሰስ ዝግጁ ናቸው።

ፈረንሣይና ዩናይትድ ስቴትስ የሚያቆራኛቸው፤ ደግሞም ጀርመንና እንግሊዝ ለዋሺንግተን ሊሸጡ የማይችሉት ነገር - ወታደራዊ ትብብር የሚባለው ነው። ይህ የጄነራልና የጄነራል ግንኙነት ጉዳይ ነው።
አሌክሳንድራ ዴ ሁፕ ሼፈር - የጀርመን ማርሻል ፈንድ የሚባለው በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ መካከል መተባበርን ለማጠናከር የሚሠራው ወገናዊ ያልሆኑ የሃሣብ አብላዮች ጠቢባን አሜሪካዊ የሕዝብ ፖሊሲ ቡድን የፓሪስ ቢሮ ዳይሬክተር

ፈረንሣይና ሌላዪቱም አውሮፓ የበረቱ ሥጋቶችን የሚያሳዩባቸው መስኮች አሉ፤ ዋሺንግተን እኮ አንዳንድ የአውሮፓ ሃገሮችን ከአዳዲስ ታሪፎቿ ውጭ ለማድረግ ከያዘችው አቋሟ ታፈነግጥ ይሆናል፤ ከኢራን የኒኩሌር ውልም ትወጣ ይሆናል ...

“የኢራንን የኒኩሌር ስምምነት ምን እናድርገው በሚል ጉዳይ ላይ በሚስተር ማክሮን እና በሚስተር ትረምፕ መካከል ዛሬ ያለው አለመስማማት በእውኑ ግዙፍ ነው” ብለዋል ዴፋርገስ።

ኢራንን በተመለከተ ሁለቱ መሪዎች ልዩነቶቻቸውን እያጠበቡ ነው የሚል ዕምነት ያላቸው አሉ፤ በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ሊቀራረቡ ይችላሉም ይላሉ።

እንግዲህ ነገር እንዲህ ካማረና አምሮበትም ከተፈፀመ ሁለቱም ሰዎች ልክ ባለፈው ሐምሌ ከባስቲይ ቀን ማግስት እንደሆነው ሁሉ፤ የፊታችን ረቡዕ ማታ ወይም ሐሙስ ማለዳ ላይ በፈገግታና በፍቅር ተጨባብጠውና ተቃቅፈው ሊሸኛኙ ይችላሉ ... ፊኒ ..

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የትረምፕና የማክሮን ኅብረት ይሰምር ይሆን?
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:44 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG