የደቡብ ካሊፎርኒያ ባለሥልጣናት ባላፈው ቅዳሜ ምሽት ዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ከሚያደርጉበት አቅራቢያ ባለ የፍተሻ ቦታ አንድ የኔቫዳ ነዋሪ በመኪናው ውስጥ ጠመንጃ፣ ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ እና ጥይቶችን ከበርካታ የሀሰት ፓስፖርቶች ጋር ይዞ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል፡፡
የሪቨርሳይድ አውራጃ የፖሊስ አዛዝ ቻድ ቢያንኮ ትላንት እሁድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቨርን ሚለር የተባለው የ49 ዓመቱ የላስ ቬጋስ ነዋሪ በአካባቢው ፖሊሶች የተያዘው፣ ወደ ምርጫው ቅስቀሳ ሥፍራ መኪና ሲያሽከርክር በአቅራቢያው በሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ ላይ ነው፡፡
“ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች ታይተው ነበር። የአካባቢው ፖሊስ መኪናው ውስጥ በጣም የተዘበራረቀ ነገር መኖሩን ተመልክቷል።” ያሉት ቢያንኮ “ ተሽከርካሪው ሃሰተኛ ሰሌዳ እንደነበረው ግልጽ ስለነበር ያ ፖሊሱ ግለሰቡ ለምን እዚያ ቦታ እንደተገኘ የምርመራ ጥያቄ እንዲያነሳ አድርጓል፡፡” ብለዋል፡፡
የፖሊስ መምሪያው በመግለጫው እንዳስታወቀው ግለሰቡ የተያዘው የተቀባበለ መሣሪያ እና በርካታ ጥይቶችን ሊጎርስ የሚችል ካርታ ይዞ እንደተገኘ በመጠርጠሩ ነው፡፡
ተጠርጣሪው በ5,000 ዶላር ዋስ የተፈታ ሲሆን እኤአ ጥር 2 ቀን 2025 ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀጠሮ ተይዟል።
በቅርብ የተቃጡ ሁለት የግድያ ሙከራዎችን ተከትሎ በትረምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በሚካሂዱባቸው ቦታዎች የደህንነት ጥበቃው እጅግ ጥብቅ ሆኗል፡፡
ባለፈው ወር ባለሥልጣናት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ለመግደል ፍላጎት እንዳለው በመጻፍ እና ፍሎሪዳ ውስጥ ለ12 ሰዓታት ተከታትሎ ሲያደባ ቆይቷል ያሉት አንድ ግለሰብ የግድያ ሙከራ ክስ ተመስርቶበታል፡፡
የፍሎሪዳው ተጠርጣሪ የተያዘው ትረምፕ በፔንሰልቬንያው የምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ በተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ በጥይት ተመትተው ጆሮአቸው ላይ ከቆሰሉ ሁለት ወራት በኋላ ነው።
መድረክ / ፎረም