የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ኢራቅ ውስጥ ግዳጅ ላይ የሚገኙ ወታደሮቻቸውን ቀደም ሲል ባልተነገረ ድንገተኛ ጉብኝት ትናንት መካከላቸው ተገኝተው ካነጋገሩ በኋላ ዛሬ ዋሺንግተን ገብተዋል።
ትረምፕ ዋይት ሃውስ ከገቡ አንስቶ በግጭት ቃጣና ውስጥ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ እጅግ በጠነከረ ምሥጢር ተዘጋጅቷል የተባለ ጉብኝታቸው የመጀመሪያቸው ነው።
ትረምፕ ዋሺንግተን ከደረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት ኢራቅና ጀርመን ውስጥ የሚገኙ ሠራዊቶቻቸውን አይተው መመለሳቸውን ገልፀው “አንድ ነገር እርግጥ ነው፤ ሃገራችንን የሚወክሉ፣ ማሸነፍ እንዴት እንደሚቻል የሚያውቁ እጅግ ድንቅ ሰዎች አሉን” ብለዋል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ ትናንት ምሽት ላይ በትዊተር ባሠራጩት መልዕክት ትረምፕና ቀዳሚት እመቤት ሜላኒያ ትረምፕ “ወታደሮቻችንንና ከፍተኛ የጦር መሪዎችን ለመጎብኘት፣ ለአገልግሎታቸው፣ ለስኬታቸው፣ ለመስዋዕትነታቸው ምሥጋና ለማቅረብ፤ እንዲሁም መልካም ገናን ለመመኘት በገና ሌሊት ከዋሺንግተን ተነስተዋል” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ትረምፕ ኢራቅ ላሉት ወታደሮቻቸው ንግግር ባደረጉበት ወቅት “እሥላማዊ መንግሥት ጨርሶ ሊሸነፍ በጣም ተቃርቧል፤ የከሊፋው መንግሥት የለም” ሲሉ ከሦሪያ የመውጣት ሃሣባቸውን አጠናክረዋል።
ወደ ሦሪያ “ከስምንት ዓመት በፊት ለሦስት ወራት ገብተን ተመልሰን መውጣት ተስኖናል” ያሉት ትረምፕ ሃሣባቸው አይሲስን ከወታደራዊ ጠንካራ ይዞታዎቹ ማስወጣት እንደነበረና የቡድኑን ርዝራዦች ከአካባቢው ጠራርጎ ለማጥፋት ቱርክ መስማማቷን አስታውቀዋል።
ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቻቸው ከሦሪያ “ሥርዓት ባለው መንገድ” ባሉት ሁኔታ እንደሚወጡ ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ