የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ "ዋይት ሃውስን ለቀው ሲወጡ፣ ሚስጥራዊ የመንግሥት ሰነዶችንም ይዘው ወጥተዋል" ሲል ፍሎሪዳ የሚገኝ የፌዴራል ፍርድ ቤት ክሥ አቅርቦባቸዋል።
የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ክሱን ለትረምፕ ጠበቆች ያስታወቀ ሲሆን፣ ትረምፕም መከሰሳቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው አረጋግጠዋል።
“በሚያሳዝን ሁኔታ አገሪቱ ቁልቁል እየሄደች ነው። በታሪክ ከየትኛውም ተመራጭ ፕሬዚደንት ከፍተኛ ድምጽ ያገኘ ሕዝባዊ ፕሬዚደንት ላይ ክስ አቅርበዋል። እኔ ንጹሁ ሰው ነኝ” ብለዋል ትረምፕ፡፡
የትረምፕ ጠበቃ ጄምስ ትረስቲ ለሲኤን ኤን እንደተናገሩት ፣ ሆን ብሎ የብሔራዊ ጸጥታ መረጃዎችን መያዝ፣ የሐሰት ቃል መስጠት እና በመንግሥት ላይ ማሴር የሚሉት ከክሶቹ ውስጥ ይገኙበታል።
የቀድሞው ፕሬዚደንት በፍሎሪዳ በሚገኘው ፍ/ቤት ማክሰኞ እንደሚቀርቡ እና የክሶቹም ብዛት ሰባት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኞች ለአሶሽየትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ክሡ ትረምፕን በአሜሪካ ታሪክ ከሥልጣን ዘመን በኋላ የተከሰሰ የመጀመሪያው የቀድሞ ፕሬዚደንት ያደርጋቸዋል። የፌዴራሉ ምርመራ ቢሮ ሰዎች ባለፈው ነሐሴ ማር አ ላጎ የሚገኘውን የትረምፕ ቤት ሲፈትሹ፣ ከ100 በላይ ሚስጥራዊ ሰነዶችን አግኝተዋል። ከሰነዶቹ ጋር በተያያዘ ምንም ጥፋት እንደሌለባቸው ትረምፕ ይናገራሉ።