በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትራምፕ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተመሰረተው ታሪካዊ ክስ እየታየ ነው


የአሜሪካ ብሄራዊ ዘብ ወታደሮች የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻን ሲጠብቁ እኤአ ጥር 13/2021.
የአሜሪካ ብሄራዊ ዘብ ወታደሮች የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻን ሲጠብቁ እኤአ ጥር 13/2021.

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሠረተው ሁለተኛው ታሪካዊው ክስ ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ በአሜሪካ ህግ መወሰኛው ምክር ቤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ትራምፕ የተከሰሱት የህግ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት የፕሬዚዳንት ባይደንን አሸናፊነት የሚያረጋግጠውን የ2020 የምርጫ ውጤት እንዳያጸድቁ ለማስገደድ፣ ከአንድ ወር በፊት፣ ደጋፊዎቻቸው በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ ያካሄዱትን የአመጽ ተቃውሞ አነሳስተዋል በሚል ነው፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕን ለክስ ያበቃው ተቃውሞ ወደ ሁከት የተቀየረው 800 የሚደርሱት የአመጹ ተሳታፊዎች የምክር ቤቱን ህንጻ ጠባቂዎች ሰብረው በማለፍ ህንጻውን ከወረሩ በኋላ ነበር፡፡

አመጸኞቹ የበር መዝጊያዎችን በመደብደብ ፣ መስኮቶችን በመሰባበር ከፖሊሶች ጋር ግብግብ በመፍጠር ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላም የአንዳንድ የምክር ቤት አባላትንም ቢሮዎች ዘርፈዋል፡፡

በሁከቱም አንድ የምክር ቤቱ ጠባቂ ፖሊስን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሞተዋል፡፡

የጠባቂው ፖሊስ አሟሟትና በሁከቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ከፖሊስ በተተኮሰባት ጥይት ህይወቷ ያለፈው የአንዲት ሴትም ጉዳይ እየተጣራ መሆኑም ተነግሯል፡፡

100 የሚሆኑት የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት፣ አምሳ ዴሞክራትና አምሳ ሪፐብሊካን በመሆኑ እኩል በተጋሩት ምክር ቤት የአንድ ዙር ብቻ ፕሬዚዳንት በሆኑት ትራፕም ላይ በቀረበው ክስ ለመስማማት የተለየ ሁኔታ ገጥሟቸዋል፡፡

ምክንያቱም ብዙዎቹ የምክር ቤት አባላት እኤአ ጥር 6 የተካሄደው አመጽ ሲካሄድ በስፍራው ነበሩ፡፡ የራሳቸውን ህይወት ለማትረፍ የተሯሯጡበትም ስለነበር በስፍራው የነበሩ እማኞች ናቸው፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት በትራምፕ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ለማሳለፍ የሚያስፈልገው ድምጽ ሁለት ሶስተኛ ነው፡፡ 50ዎቹ ዴሞክራቶች ውሳኔውን እንደሚደግፉ ሲታሰብ ከሪፐብሊካኖቹ ቢያንስ 17 የሚሆኑት ትራምፕን ተቃውመው ድምጽ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ትራምፕ ባለፈው ዓመት የምርጫው ተፎካካሪያቸው በነበሩት በጆ ባይደን ላይ ጥፋት እንዲያፈላልጉ፣ የዩክሬይን ፕሬዚዳንትን አግባብተዋል በሚል በተከሰሱበት የመጀመሪያው ተመሳሳይ ክስ በነጻ እንደተሰናበቱት ሁሉ በዚህኛም ነጻ እንደሚወጡ ይገመታል፡፡

ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ትራምፕ ፣ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ በሆነው የአሜሪካ ታሪክ ውስጥ፣ ሁለት ጊዜ ከሥልጣናቸው እንዲሰናበቱ ክስ የተመሰመረተባቸው ብቸኛው ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡

የዩናይድ ስቴትስ ተወካዮች ምክር ቤት 232-197 በሆነ ድምጽ ፕሬዚዳንት ትራምፕን በጥፋተኝነት እንዲከሰሱ የወሰነው የምክር ቤቱ ህንጻ በሁከት ከተናወጠ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ ትራምፕ አመጹን በማነሳሳት ተጠያቂ ናቸው ካሉት 222 ዴሞክራቶች ጋር የተባበሩት 10 ሪፐበሊካን አባላት ናቸው፡፡

ትራምፕ በተከሰሱበት ጉዳይ በአካል ተገኝተው መከላከያቸውን እንዲያሰሙ በዴሞክራቶቹ የቀረበላቸውን ጥያቄ ያልተቀበሉት ሲሆን ያንን ማድረግ የማይጠበቅባቸው መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ክርክሩን የሚያደምጠው ችሎት አንድ ሳምንት ምናልባትም ከዚያ በበላይ ሊቆይ እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የክስ ሂደቱን የሚመሩትና በትራምፕ ላይ የመሰረቱትን ክስ የሚያሰሙት 9 የዲሞክራቲክ ምክር ቤት አባላት ሲሆኑ ብዙዎቹ ቀደም ሲል ዐቃቢያነ ህጎች የነበሩ ናቸው፡፡

“ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫው የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ደጋፊዎቻቸው በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ በማነሳሳታቸው “በተጠናጥል ተጠያቂ ናቸው” በማለት ይከራከራሉ፡፡

እኤአ ጥር 6 ትራምፕ በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት የነበሩ ደጋፊዎቻቸው ወደ ምክር ቤቱ ህንጻ በመገስገስ እጅግ በተቆጣ ስሜት ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ ማነሳሳታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ምንም የተጨበጠ ማስረጃ ሳያቀርቡ ምርጫው የተጭበረበረ መሆኑንም በመናገር ደጋፊዎቻቸውን አስቆጥቶ በማነሳሳት ተከሰዋል፡፡

አንድ ሰዓት በላይ በፈጀው ንግግራቸው አንድ ጊዜ ብቻ “ተቃውሞችንን ሰላማዊና አርበኝነት በተቀላቀለበት መንገድ ማሰማት ይኖርብናል” ማለታቸውም ተመልክቷል፡፡

ትራምፕ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተመሰረተው ታሪካዊ ክስ እየታየ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:17 0:00

ይሁን እንጂ አስከትለውም “ሁላችሁም እዚህ የመጣችሁት ምርጫው እንዳይሰረቅ ለመታገል ነው፡፡ ስለዚህ “አገራችን ክበቂ በላይ አይታለች፡፡ ካሁን በኋላ ግን በቅቶናል፡፡ በኃይል አክርራችሁ መታገል ይኖርባችኋል፡፡ አምርራችሁ ካልታገላችሁ አገር አይኖራችሁም፡፡” ማለታቸውም ተስምቷል፡፡

ብዙ ልምድ ያላቸው የትራምፕ ጠበቆች የሆኑት ደቪድ ሾን እና ብሩስ ካስተር በበኩላቸው፣ ትራምፕ ከአሁን በኋላ ፕሬዚዳንት ስላልሆኑ ከሥልጣናቸው ሊወገዱ ይገባል የሚለው ክስ አይመለከታቸውም፣ ስለዚህ ክሱ ህገ መንግስታዊ አይደለም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

ከሳሾቹ ደግሞ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት ግን ይህን መሰሉን ክስ ከዚህ ቀደም በ1876 መስተናገዱን በመጥቀስ ሥልጣን መልቀቅ ከሠሩት ወንጀል ነጻ የሚያወጣ ሽፋን አይደለም ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የተወካዮቹ ምክር ቤት ተከራካሪዎች ትራምፕ ክስ እንዲመሰረትባቸው በተወካዮቹ ምክር ቤት የተወሰነው ገና በሥልጣን ላይ እያሉ ስለሆነ መከሰሳቸው አግባብ ነው ይላሉ፡፡

የትራምፕ ደጋፊ ከሆኑት መከካል አንዳንዶቹ የክሱ ሂደት ህገ መንግሥታዊ አለመሆኑን በመጥቀስ መታየት የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ50ዎቹ ሪፐብሊካን መካከል 5ቱ ሪፐብሊካኖች ከዴሞክራቶች ጋር በመተባበራቸው ከሱ እንዲታይ ተደርጓል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ችሎቱ እማኞችን አቅርቦ ሊያነጋግር እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

የትራምፕ ጠበቆች የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከተነሳሳው አመጽ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን ማሰባሰባቸውም ተዘግቧል፡፡

እየተካሄደ ያለው ነገር የፖለቲካ ቴአትር ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፕሎሲና መሰሎቻቸው ለፖለቲካ ጥቅም ሲል የሚያካሂዱት ነው በሚል ክሱን ማጣጣላቸውም ተሰምቷል፡፡

ዴሞክራቶቹም ተከራካሪዎች በበኩላቸው “የምንኖረው በህግ በሚመራ አገር ውስጥ ነው እንጂ በምርጫ የደረሰባቸውን ሽንፈት መቀበል በማይችሉ ፕሬዚዳንት በሚነሳሳ አመጽና ነውጥ አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ ህዝብ የገቡትን ቃል ክደው የፈጸሙት ግልጽ ተጠያቂነት አለ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

(ዘገባው ከቪኦኤ ዘጋቢ ከኬን ብሬድሜየር የተገኘ ነው)

XS
SM
MD
LG