የዩናይትድ ስቴትስ የመወሰኛ ምክር ቤት በዶናልድ ትረምፕ ላይ የተመሰረተውን ክስ በቀጣዩ ሳምንት መስማት ይጀምራል።
እአአ የካቲት 9/2021 አንድ መቶዎቹም የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ተሰይመው በቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ የተመሰረተውን ክስ ማድመጥ ይጀምራሉ።
የቀድሞው ፕሬዚደንት ትረምፕ ደጋፊዎች ጆ ባይደን ያሸነፉበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንዲሰረዝ ለማድረግ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትን በመውረር የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤቱ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያቀረበባቸውን አመጽ የመቀስቀስ ክስ ወደመወሰኛ ምክር ቤቱ መርቶታል።
በዚህም ዶናልድ ትረምፕ ሁለት ጊዜ በምክር ቤት የተከሰሱ ብቸኛው ፕሬዚዳንት ሆነዋል። ትናንት የክሱ ዶሴ አቅራቢዎች መሪው የሜሪላንዱ ዲሞክራቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ጄሚ ራስኪን፤ ዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎቻቸው ካፒቶሉን በወረሩበት ዕለት ምን እንዳደረጉ የመወሰኛ ምክር ቤቱ ክስ ሰሚ ችሎት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመው ቃላቸውን እንዲሰጡ በደብዳቤ ጠይቀዋል። ሁለቱ የትረምፕ ጠበቆች ፈጥነው ጥያቄውን ለታይታ የሚደረግ ነው፣ አንቀበልም ብለዋል።
በቀጣዩ ሳምንት የመወሰኛ ምክር ቤቱ ችሎት ሲጀመር በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ውጤት የተናደዱ ጽንፈኞች ቁጣቸው ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት አለ። በዚህም ምክንያት መዲናዋ ዋሽንግተን ውስጥ እና አካባቢዋ የጸጥታ ሃይሎችን እና ፖሊሶች በከፍተኛ ደረጃ ዝግጁ ሆነው ጥበቃ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።