በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትራምፕ ክስ የአመጽ ጥቃቱን ሂደት የሚያሳዩ የምስል ማስረጃዎች ቀረቡ


ከቀደሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግሮችና ከፖሊስ ካሜራዎች የተገኙ ምስሎችን ክሱን ከሚመሩት ሴነተሮች አንዱ የሆኑት የቴክሳሱ ዴሞክራት ጃክዊን ካስትሮ በምክር ቤቱ ሁለተኛው ቀን ችሎት ላይ ባሰሙት ንግግር ተጠቅመውባቸዋል
ከቀደሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግሮችና ከፖሊስ ካሜራዎች የተገኙ ምስሎችን ክሱን ከሚመሩት ሴነተሮች አንዱ የሆኑት የቴክሳሱ ዴሞክራት ጃክዊን ካስትሮ በምክር ቤቱ ሁለተኛው ቀን ችሎት ላይ ባሰሙት ንግግር ተጠቅመውባቸዋል

በቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የተመሰረተውን ክስ የሚመሩት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የትራምፕ ደጋፊዎች እኤአ ጥር 6 በምክር ቤቱ ህንጻ ስላካሄዱት አመጽ፣ ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ የቪዲዮ ምስሎችን፣ በትናንትናው የምክር ቤቱ ችሎት በማስረጃነት አሳይተዋል፡፡

የቪዲዮ ምስሎቹ ዴሞክራቶቹ በመጀመሪያው የችሎት ውሏቸው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ በየከፍለ ግዛቱ ተወካዮች የተሰጠውንና፣ የጆ ባይደንን አሸናፊነት የሚያረጋግጠውን የምርጫ ውጤትና ሂደት ለመቀልበስ ለተካሄደው አመጽ፣ በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸውን ያሳዩበት ነው፡፡

ይህ ሲፈጸም የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስና የምክር ቤቱ አባላት የአመጽ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ጥቂት እልፍ ብለው ነበር የሚገኙት፡፡ እነሱን ለመካከል የቆሙት ፖሊሶች በወራሪዎቹ አመጸኞች ተደብድበዋል፡፡

በትራምፕ ክስ የአመጽ ጥቃቱን ሂደት የሚያሳዩ የምስል ማስረጃዎች ቀረቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:51 0:00

እኤአ ጥር 6 በምክር ቤቱ ህንጻ የተካሄደውን ጥቃት የሚያሳዩት የቪዲዮ ምስሎች በትላንቱ ችሎት ቀርበዋል፡፡

ክሱን የሚመሩት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አመጹን በማነሳሳት በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸውን ለማሳየት የመክፈቻ ክርክራቸውን ያቀረቡት እነዚህም ምስሎች በማሳየት ነበር፡፡

ክሱን ከሚመሩት መካከል የምክር ቤት አባል ጄሚ ራስኪን እንዲህ ይላሉ

“ተከሳሹ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በምንም መመዘኛ ከጥፋቱ ነጻ አለመሆናቸውን እናረጋግጣለን፣ የፈጸሙት ድርጊት ጨርሶ ያልተገባ ስለሆነ ለመጭው ፕሬዚዳንቶችም መመዘኛ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህን ጥቃት ያነሳሱት እኚህ ፕሬዚዳንት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ያውቁ ነበር፡፡”

ክሱን የሚመሩት የምክር ቤቱ አባላት፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ “የምርጫውን ስርቆት አቁም!” በሚል መፈክር፣የተካሄደውን ዘመቻ መምራት የጀመሩት አመጹ ከመካሄዱ በፊት ነው በማለት ይከራከራሉ፡

ምርጫው የተጭበረበረ መሆኑን በመግለጽ ደጋፊዎችን ለአመጽ በማነሳሳት የምርጫውን ሂደት እንዲያጠቁ ማድረጉ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡

ዴሞክራቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ኤሪክ ስዋል ዌል እንዲህ ይላሉ

“ይህ የአንድ ንግግር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህን የአመጽ መንጋ ለወራት በተደጋገመ ንግግራቸው ሲያዘጋጁት ነው የኖሩት፡፡ በምርጫው የሰጡት ድምጽ የተሰረቀባቸው መሆኑን እስኪያምኑ ድረስ ስለሆነ የተነገራቸው የምርጫውን ውጤት የማረጋገጡን ሂደት ለማቆም ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡”

ትራምፕ ምርጫውን አስመልክቶ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ያቀረቡት ክስ አመጹ ከመካሄዱ ሳምንታት በፊት ውድቅ ተደርጓል፡፡

ይህን የሚሉት ዴሞክራቷ የምክር ቤት አባል ማድላይን ዲን ናቸው፡፡ እንዲህ ብለዋል

“አንድም ፍርድ ቤት፣ አንድም ዳኛ የምርጫው ውጤት ተቀባይነት የለውም ወይም ማረጋገጫው ሊሰጠው አይገባም አላለም፡፡”

የቀደሞው ፕሬዚዳንት የጆባይደንን አሸናፊነት የሚያረጋግጠውን የምርጫ ሂደት ለማደናቀፍ ያደረጓቸውን ጥረቶች ሁሉ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ዴሞክራቷ የምክር ቤት አባል ስቴሲ ፕላስኬት እንዲህ ብለዋል

“ለፕሬዚዳንት ትራምፕ የአመጹ ውጤት ጨርሶ የማይታያቸው ሆኖ አይደለም፡፡ እሱ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የአመጹ ጥቃት እንዲፈጸም እሳቸው ሆን ብለው የገፋፉት ነገር ነው፡፡”

የፕሬዚዳንቱ ጠበቆች መከላከያቸውን የፊታችን ዓርብ ያሰማሉ፡፡ “ትራምፕ የንግግር ነጻነታቸውን ተጠቅመው ሀሳባቸውን ገለጹ እንጂ ለአመጹ ተጠያቂ አይደሉም” በማለትም ይከራከራሉ፡፡

ምንም እንኳ ተቸዎች፣ የትራምፕ ጠበቆች የክርክራቸውን ጭብጥ በአግባቡ ለማቅረብ ተቸግረዋል ቢሉም፣ ትራምፕ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ይሰጣል የሚል እምነት ግን የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በውሳኔው ላይ ቢያንስ 17 የሪፐብሊካን አባላት ከዴሞክራቶቹ ጋር መተባበር አለባቸው፡፡

ከብሩኪንግ ተቋም ጃን ሁዳክ እንዲህ ይላሉ

“ራሳቸውን ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ተገዥ አድርገዋል፡፡ የራሳቸው የወደፊቱ የፖለቲካ እጣ ለምክር ቤቱ ምርጫ በሚወጡ በእሳቸው ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በተለይም የሪፐብሊካን ክፍለ ግዛቶች በሆኑ አካባቢዎች ያሉት ይህ ስጋት አለባቸው፡፡ ስለዚህ በተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው ማስረጃው የቱንም ያህል እንኳ ቢሆን፣ አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች ማስረጃዎቹን ችላ በማለት፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት በነጻ ያሰናብታሉ፡፡”

ትራምፕ ካሁን በኋላ ተመልሰው ለፌደራል ሥልጣን የመወዳደር እድላቸው አጠየያቂ ቢሆንም፣ ክሱን የመሰረቱት የምክር ቤት አባላት፣ የክስ ጭብጣቸውን ለማሰማት በዛሬው እለት የስምንት ሰዓታት ጊዜ አላቸው፡፡

(በምክር ቤቱ የቪኦኤ ዘገባ ካትሪን ጊፕሰን ካጠናቀረቸው የተወሰደ)

XS
SM
MD
LG