በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ምክር ቤቱ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲከሰሱ ወሰነ


በዴሞክራቲክ ፓርቲ በላይነት ሥር ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት፣ ትላንት ረቡዕ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንዲከሰሱ ወስኗል፡፡

የውሳኔው ምክንያት፣ ፕሬዚዳንቱ፣ ባለፈው ሳምነት ከየክፍለ ግዛቱ ተወካዮች የተገኘውን የምርጫ ውጤት፣ ቆጥሮ ለማጽደቅ፣ በምክር ቤቱ የሚደረገውን የማረጋጋጫ ሂደት በማደናቀፍና ውጤቱንም በአመጽ ኃይል ለመቀልበስ የማነሳሳት ሙከራ አድርገዋል የሚል ነው፡፡

ውሳኔው በሌላኛው የእንደራሴዎች ምክር ቤትም የሚታይ ቢሆንም፣ ይህ ግን ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በዓለ ሲመታቸውን እስከሚፈጽሙበት የሚቀጥለው ሳምንት ድረስ፣ የሚሆን አይደለም፡፡

የምክር ቤቱ አባላት፣ ባላፈው ሳምንት፣ የተመራጩን ፕሬዚዳንት ባይደን አሸናፊነትን ለመቀለበስ፣ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ለቀው እንዲወጡ ከተገደዱበት፣ እዚያው የምክር ቤት ህንጻ ውስጥ ሆነው ነው፣ ውሳኔውን ያሳለፉት፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት 232 ለ 197 በሆነ ድምጽ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንዲከሰሱ ወስኗል፡፡

ለውሳኔ የተሰጠው ብቸኛው ምክንያት፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ እኤአ ጥር 6፣ በምክር ቤቱ ላይ የተቃጣውን አመጽ አነሳስተዋል በሚል ነው፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሥራቸውን በብቃት ማከናወን በሚችሉብት ሁኔታ ላይ አይደሉም በሚል፣ ከሥልጣናቸውን እንዲነሱ የሚያዘውን ህግመንግስታዊ አንቀጽ፣ ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይሹ አስታውቀዋል፡፡

ምክር ቤቱም፣ ትራምፕ እንዲከሰሱ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይህንኑ አቋማቸውን፣ ለተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ፣ ካሳወቁ በኋላ ነው፡፡

በብሄራዊ ዘብ አባላት፣ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ከሚገኘው የምክር ቤት ህንጻ የተላለፈውን ውሳኔ የመሩት፣ አፈጉባኤ ናነሲ ፐሎሲ እንዲህ ብለዋል

“ፕሬዚዳንቱ፣ ሥልጣንን በኃይል ሊገለብጡ የተነሱ አመጸኞችን የተመለከቷቸው የነጻነት ጠላት አድርገው አይደለም፡፡ ይልቁንም የአደገኛ ግባቸው መጠቀሚያ አድርገው ነው የወሰዷቸው፡፡ ግባቸው የግላቸውን ሥልጣን የመጨበጥ፣ የህዝብን ፈቃድ የመገልበጥ ግብ ነው፡፡ ግባቸው፣ ከሁለት ምዕተ ዓመት ከግማሽ በላይ የቆየውን ዴሞክራሲያችንን፣ ባቀጣጠሉት ደም አፋሳሽ አመጽ እንዲያልቅ የማድረግ ግብ ነው፡፡”

አብዛኞቹ የሪፐብሊካን ምክር ቤት አባላት፣ ፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እስከመጠየቅ የሚያደርስ ጥፋት አልፈጸሙም ባይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን ግን፣ ፕሬዚዳንቱ፣ በአመጹ ውስጥ የራሳቸው ድርሻ እንዳለቸው ያምናሉ፡፡

በተወካዮች ምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቭን መካርቲ እንዲህ ይላሉ

“ባለፈው ረቡዕ በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ በአመጸኞቹ መንጋ ለተፈጸመው ጥቃት ፕሬዚዳንቱም ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ ጥቃቱን ማውገዝ የነበረባቸው እየሆነ ያለውን ነገር እንደተመለከቱ፣ ወዲያውኑ ነበር፡፡”

በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ፣ ሁለት ጊዜ በመከሰስ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የመጀመሪያው ይሆናሉ፡፡ ትራምፕ ግን፣ ከአመጹ በፊ ያደረጉት ንግግራቸውን አሁንም ቢሆን ምንም ችግር እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡

በበኩላቸውም በደጋፊዎቻቸው የተካሄደውን አመጽ አውግዘዋል፡፡

“እውነተኛ ደጋፊዬ የሆነ ማንም ሰው የፖለቲካ አመጽን አይደግፍም”” ብለዋል ትረምፕ፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳይከሰሱ ከዴሞክራቶች ጋር የተባበሩት 10 የሪፐብሊካን አባላት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፣ በፓርቲው ውስጥ ትልቅ ተሰሚነት ያላቸው ሊዝ ቼኒ ይገኙበታል፡፡ ቼኒ ፕሬዚዳንቱ የፈጸሙት እንደ ትልቅ ክህደት የሚቆጠር ነው በማለት ኮንነዋቸዋል፡፡

በተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ፣ እንደገና ወደ ሌላኛው እንደራሴዎች ምክር ቤት በመሄድ መታየት ይኖርበታል፡፡ በዚህኛውም ምክር ቤት፣ አንዳንድ የሪፐብሊካን እንደራሴዎች፣ በፕሬዚዳንቱ የመከሰስ ውሳኔ ዲሞክራቶቹን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በብሩኪንግ ተቋም ተማራማሪ የሆኑት ኤሌን ካምራክ ግን፣ የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በሪፐብሊካን ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል ባይ ናቸው፡፡ እንዲ ብለዋል

“በሚቀጥሉ ቀናት ውስጥ በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ ከበድ ያለና የሚያስቀይም ጥቃት የሚሰነዘር ከሆነ፣ ያ ፍርዱን ለመስጠት የበለጠ ያነሳሳል፡፡ ለነገሩ የሚሆነው፣ ውጥረቱ እየበረደ ይመጣል፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ፣ ሴነተሮቹ ፕሬዚዳንቱ ላይ እስከመፍረድ ድረስ ርቀው መሄዱን ላይፈልጉት ይችላሉ፡፡”

የሴነቱ መሪ ሚች መካኔል፣ ምክር ቤታቸው ጉዳዩን ተመራጩ፣ ጆ ባይደን በዓለ ሲመታቸውን ከመፈጸማቸው በፊት እንደማይመለከተው ተናግረዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ቢሆን ምክር ቤቱ፣ ለፕሬዚዳንት ባይደን አጣዳፊ አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል፡፡

አሁንም ከብሩኪንግ ተቋም ኤለን ካምራክ እንዲህ ይላሉ

“ ያ ለባይደን መጥፎ አጋጣሚ ነው፡፡ ለአገራችንም እንዲሁ አለመታደል ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ሁላችንም የምንጠብቀው አንድ ነገር ቢኖር ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡”

በመራጭነት ከተመዘገቡት የተሰበሰቡት የህዝብ የአስተያየት ድምጾች እንደሚያሳዩት፣ 56 ከመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን፣ በምክር ቤቱ ላይ ለተነሳው አመጽ ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተጠያቂ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡

በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ፣ ጥፋተኛ ከተባሉ፣ ካሁን በኋላ በየትኛውም የፌደራል መንግሥት ኃላፊነት እንዳይወዳደሩ ያግዳቸዋል፡፡

ዘገባው የቪኦኤ የምክር ቤት ዘጋቢ፣ ካትሪን ጊብሰን ነው፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

ምክር ቤቱ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲከሰሱ ወሰነ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:57 0:00


XS
SM
MD
LG