የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአራት ዓመት የሥራ ዘመን በዛሬው እለት ተጠናቋል፡፡
“አሜሪካንን ወደ ታላቅነቷ እንመልሳት” በሚል መሪ መፈክር ወደ ዋይት ሀውስ የመጡት ትራምፕ፣ ስለ ወደፊቱ እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ወደ ደቡባዊቷ የፍሎሪዳ ግዛት ሄደዋል፡፡
ትራምፕ ዛሬ ማለዳው ላይ፣ ዋይት ሀውስን ለቀው ሲወጡ የአገልግሎታቸውን ዘመን
“በህይወት ዘመን ሁሉ የሚሰማ ክብር” ብለውታል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ወደ ፍርሎሪዳ ለመብረር ከመነሳታቸው በፊት ሜሪላንድ በሚገኘው አንድሩ አየር ኃይል የጦር ሰፈር መጠነኛ አሸኛነት ተደርጎላቸዋል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ በተሳፈሩበት ቁጥር አንድ አውሮፕላን (ኤር ፎርስ ዋን) ተሳፍረው ነበር ወደ ፍሎሪዳ ያቀኑት፡፡
ትራምፕ ዋይት ሀውስን ለቀው የወጡት በዋሽንግተን ዲሲ ሰዓት አቆጣጠር፣ ዛሬ ረቡዕ ጥር 20/2021፣ ከጧቱ 2 ሰዓት ከሩብ ላይ ነበር፡፡
ከዋይት ሀውስ፣ ሜሪላንድ ወደ ሚገኘው የአንድሩ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር የተጓዙት በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ለመጨረሻ ጊዜ በተሳፈሩበት የማሪን ዋን ሂሊኮፕተር ሆነው ነው፡፡
አንድሩ ጦር ሰፈር እንደደረሱ የተደረገላቸው የአሸኛኘት ፕሮግራም የቀይ ምንጣፍ፣ በወታደራዊ ባንድ እና ለክብራቸው 21 ጊዜ በተተኮሰ መድፍ ነበር፡፡ ለሽኝቱ በስፍራው የተገኙ ሰዎች ወደ 200 የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡
ትራምፕ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ባደረጉት ንግግር
“እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ አራት ዓመት ጊዜ ነበረን፡፡ ብዙ ውጤት አስመዝግበናል” ብለዋል፡፡
ሠራዊቱን እንደገና መገንባታቸውን ጨምሮ ያስመዘገቧቸውን ታላላቅ ድሎችም ዘርዝረዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቶች ብቻ ወደሚሳፈሩበት ወደ ቁጥር አንድ ወይም ኤር ፎርስ ዋን አውፕላን ለመጨረሻ ጊዜ በመሳፈር ወደ ፍሎሪዳ አቅንተዋል፡፡
ምህረትና አመክሮ
በሌላም በኩል፣ ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻው የሥልጣን ቀናቸው ምህረትና አመክሮ ሰጥተዋል፡፡ በምህረታቸው ውስጥ ከተካተቱ መካከል የራፕ ሙዚቃ አንቃኞች ሊል ዋይኔ እና ኮዳክ ብላክ አንስቶ በምርጫው ወቅትና ኋላም በዋይት ሀውስ የፕሬዚዳንቱ ቁልፍ አማካሪ እስከ ነበሩት የ67 ዓመቱ፣ ስቲቭ ባነን ድረስ ያሉትን ያካትታል፡፡
ባነን ለዩናይትድ ስቴትና የሜክስኮ ድንበርን ላይ ለሚሰራው ግንብ ማሰሪያ ከደጋፊዎች የተሰበሰበ ገንዘብ፣ በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሱ ነበሩ፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕን አስተዳደር ለቀው የወጡት እኤአ በ2017 ሲሆን የዋይት ሀውስ አማካሪዎች ፕሬዚዳንቱን ለስቲቭ ባነን ምህረቱን እንዳይሰጡ አሳስባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም ሰዎች ምርጫው ተጭበርብሯል ከሚለውና ካልተረጋገጠው ክሳቸው ወዲህ ወዳጅነትነታቸው አንሰራርቷል፡፡
ከትላልቆቹ የሪፐብሊካን ፓርቲ ገንዘብ አሰባሳቢ፣ ባለጉዳይና ባለሥልጣናትን አግባቢ ከሆኑት ሰዎችም መካከልም አንዱ የሆኑት ኢልዮት ብሮይዲም እንዲሁ በምህረቱ የተካተቱ ናቸው፡፡
ኢልዮት ካልተመዘገቡ የውጭ ኃይላት ወኪሎች በተለይም ከቻይናና ማሌዥያን ባለጉዳዮች ጋር የትራምፕ አስተዳደርን በሚስጥር አግባብተው ለማገናኘት ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል ጥፋተኛ የተባሉ ናቸው፡፡
ሌሎች በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የተፈረደባቸው የህግ ታራሚዎችም በፕሬዚዳንቱ ምህረት የተደረገላቸው ሲሆን የእስርና የፍርድ ዘመናቸው እንዲያጥር የተደረገላቸውም ይገኙበታል፡፡
የመሰናበቻ መልዕክት
የቀድሞ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ 20 ሰዓታት ሲቀሩት በትናንትና እለት በቪዲዮ ምስል የተቀነባበረ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ፣ ቀኑን ሙሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ባሳለፉበት የትንናትው እለት፣የመሰናበቻ መልዕክታቸው ለአዲሱ አሳተዳደር ስኬት እንደሚጸልዩና መልካም እድልንም እንደሚመኙ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ ይህን ሲሉ የአዲሱን አስተዳደር ፕሬዚደንት ጆ ባይደንን ግን በስም አልጠቀሱም፡፡
ትራምፕ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ 20 ሠዓታት ሲቀሩ ባወጡት መልዕክታቸው እንዲህ አሉ፦
“በዚህ ሳምንት አዲስ አስተዳደር እንቀበላለን፡፡ አስተዳደሩ አሜሪካንን ደህንነቷ የተጠበቀና የበለጸገች በማድረጉ በኩል እንዲሳካለት እንጸልያለን ፡፡ ለአዲሱ አስተዳደርም “መልካም ምኞታችንን እናስተላልፋለን፡፡ መልካም እድልም እንመኝላቸዋለን፡፡ “እድል” የሚለው ቃል በጣም አስፈላጊ ቃል ነው ፡፡”
20 ደቂቃ በፈጀው የቪዲዮ መልዕክታቸው፣” በዓለም ኢኮኖሚ ታሪክ እጅግ የላቀው ነው” ላሉት የኢኮኖሚ ስኬት፣ ራሳቸውን ምክንያት አድርገዋል፡፡ በተለይም በአስርት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት አዲስ ጦርነት ባለመጀመር የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት መሆናቸውንም” ተናግረዋል፡፡
በዋይት ሀውስ አማካይነት በዩቱብ የተሰራጨው የትራምፕ ቪዲዮ እንደተለቀቀ፣ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ሜሪላንድ በሚገኘው አንድሩ የጦር ሰፈር ውስጥ ባለው የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ እያረፉ ነበር፡፡
አንድሩ የጦር ሠፈር ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛሬ ጥዋት የስንብት ዝግጅት ስነ ስርዐታቸውን የሚያከናውኑበት ስፍራ ነው፡፡ ከዚህ ስፍራ ፣ ቁጥር አንድ ኤር ፎርስ ዋን በሚባለው ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን ፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ወደሚገኘው መኖሪያቸው ይበራሉ፡፡
ትራምፕ የቆየውን ልማድ ጥሰዋል፡፡ የክፍለ ግዛቱን ተወካዮችንም ሆነ የመላውን መራጭ ህዝብ ድምጽ አሸንፈው በዛሬው እለት ቃለ መሃላ በሚፈጽሙት የጆ ባይደን ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ላይ አልተገኙም፡፡ በሀሰት ምርጫው የተጭበረበረ መሆኑን የሚገልጹት ትራምፕ በልማዱ መሠረት ባይደንን “እንኳን ደስ ያልዎት” አላሏቸውም፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ግን፣ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት፣ የዛሬው የባይደን በዓለ ሲመት ላይ ይገኛሉ፡፡
ምናልባት ትራምፕ ማድረግ የቻሉት ነገር ቢኖር፣ ዋይት ሀውስ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው የመኝታ ቤታቸው መስኮት ሆነው ከፊት ለፊታቸው፣ ለበዓለ ሲመቱ የተዘጋጀውን ትልቅ ምስል መመልከት ብቻ ነበር፡፡ በየቦታው የሚውለበለቡ ሰንደቅ ዐላማዎችና ትላልቅ ጽሁፎችን ያነገቡ ቅስቶች ይታያሉ፡፡ በላያቸውም በትልቁ ተጽፎ የሚነበበው ጽሁፍ “የባይደን ኻሪስ የ2021 በዐለ ሲመት” ይላል፡፡
ለበዐለ ሲመቱ የሚደረጉት የሰልፍ ትርኢቶችና ዝግጅቶች፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በጸጥታው ስጋት የተነሳ በአብዛኛው ተቀንሰው በድረ ገጾች ብቻ እንዲካሄዱ ተደርጓል፡፡
አመጹና የትራምፕ መከሰስ
የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፖሊሲ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንዲከሰሱ የተላለፈውን ውሳኔ፣ በዚህ ሳምንት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ያን ማድረጋቸው፣ ምክር ቤቱ በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ፣ ጉዳዩን በይፋ ማንቀሳቀስ እንዲጀምር ያደርገዋል፡፡
ዴሞክራቶቹ በበላይነት በሚቆጣጠሩት የተወካዮች ምክር ቤት፣ 10 የሚሆኑ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላት፣ በፕሬዚዳንቱ የመከስስ ውሳኔ ላይ ፣ከዴሞክራቶቹ ጋር ተባባሪ ሆነዋል፡፡
ትራምፕ እንዲከሰሱ፣ ውሳኔው የተላለፈባቸው፣ እኤአ ጥር 6፣ ደጋፊዎቻቸው የምርጫውን ውጤት ለመቀልበስ በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ የፈጸሙትን የአመጽ ጥቃት ገፋፍተዋል መባላቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት መሪ የነበሩት ሚች መካኔል በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ትናንት ማክሰኞ ሲናገሩ፣ እንዲህ አሉ
“የአመጽ መንጋው የሀሰት ወሬዎችን ተግቷል፣ አመጸኞቹም በፕሬዚዳንቱ እና ሥልጣን ባላቸው ሌሎች ሰዎች የተገፋፉ ናቸው”
ዴሞክራቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ ካስትሮ ቴክሳስ፣ የፕሪዚዳንቱን የመከሰስ ሂደት ከሚመሩት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ባለፈው እሁድ ለኤቢሲ የዜና ማሰራጫ ሲናገሩ
“ የዚህ ክስ አንዱ ዋና ዓላማ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ካሁን በኋላ ተመልሰው ፕሬዚዳንት ለመሆን ለፌደራል መንግሥት እንዳይወዳደሩ እርግጠኛ ለመሆን ነው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ አመጽ ያነሳሳ ሰው ተመልሶ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ምናልባት እኤአ 2024 ላይ ተመልሰው ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ትናንት ባሰራጩት የስንብት የቪዲዮ መልዕክት እንዲህ ብለዋል፦
“በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሁሉም አሜሪካውያን ደንግጠዋል፡፡ የፖለቲካ አመጽ ጥቃት እንደ አሜሪካ በምናከብራቸው ሁሉም ነገሮቻችን ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው፡፡ በፍጹም እሚታገሱት ነገር መሆን የለበትም፡፡ ነገ ረቡዕ ቀትር ላይ፣ ለአዲሱ አስተዳደር ሥልጣን ለማስረከረብ በዝግጅት ላይ በሆንኩበት በዚህ ሰዓት፣ እንድትገነዘቡት የምፈልገው ነገር፣ የጀመርነው ንቅናቄ ገና የተጀመረ መሆኑን እንድታውቁት ነው፡፡”
ትራምፕ በታሪክ
ትራምፕ ሥልጣን ሲለቁ፣ በአሜሪካ ታሪክ፣ አገሪቱን በመከፋፈል ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ፕሬዚዳንት ሆነው ነው፡፡
የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያዎች እንደሚያሳዩት፣ ምንም እንኳ አሁንም በሪፐብሊካን ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም፣ በጠቅላላው ህዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ ግን እጅግ በጣም ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በማርቲስት የህዝብ አስተያየት ድምጽ መሰብሰቢያ መሰረት፣ 16 ከመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን ትራምፕን በአሜሪካ ታሪክ እንደ ጥሩ ፕሬዚዳንት ኣድርገው ወስደዋቸዋል፡፡ 47 ከመቶ የሚሆኑት ግን ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ የከፉና መጥፎው ፕሬዚዳንት አድርገው ተመልክተዋቸዋል፡፡
ትራምፕ በመጨረሻዎቹ የፕሬዚዳንትነት ቀኖቻቸው፣ የአስፈጻሚነት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ በውጭ አገር የተሰሩ በራሪ ድሮኖች መግዛትን ከመገደብ አንስቶ፣ በአሜሪካ የሰማዕታት መታሰቢያ የአትክልት ስፍራዎች ላይ፣ ሀውልት የሚቆምላቸው ጀግኖችን እስከመሰየም ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በዛሬው ዕለት ቃለ መሃላቸውን የፈጸሙት 46ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ሥልጣን እንደያዙ በትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣን የተላለፉ በርካታ ውሳኔዎችን ይሽሯቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(በተለያዩ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች ከተጠናቀሩ ዘገባዎች የተዘጋጀ)