በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ደነገጉ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ደነገጉ።

ፕሬዚዳንቱ እርምጃውን የወሰዱት በሃገራቸው የደቡብ ድንበር ላይ አቆመዋለሁ ብለው በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ቃል ገብተውበት ለነበረ የግንብ አጥር የሚውል ገንዘብ ለማውጣት እንዲያስችላቸው መሆኑ ታውቋል።

ይሁን እንጂ ከዴሞክራቲክ ፓርቲው በአጠቃላይና ከራሳቸውም ሪፐብሊካን ፓርቲ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ እንደራሴዎች ይህንን ውሣኔአቸውን እንዳልወደዱላቸው ይሰማል።

ይህንን ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ እርምጃቸውን በፍርድ ቤት እንደሚያሳግዱና እንደሚሞግቱም ተቃዋሚዎቻቸው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ታውቋል።

ፕሬዚዳንቱ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውን እንዲጥሉ የገፋቸውን ምክንያት ሲናገሩ “ ‘አራዊት ወሮበሎች’ ሲሉ የጠሯቸው ቡድኖችና አደንዛዥ ዕፅዋትና ቅመማ ቅመም እንዲሁም የሕገወጥ ፍልሰት ግዙፍ ቅፍለት ሃገሪቱን እየወረሩና እያጥለቀለቁ በመሆናቸው ነው” ብለዋል።

ትረምፕ አክለውም መንግሥቱን ዛሬ እኩለ-ሌሊት ላይ ይጠብቀው የነበረውን ሌላ ከፊል መዘጋት በሚያስቀር ውሣኔ የሁለቱም ፓርቲዎች አባላት የሆኑ እንደራሴዎች ሰሞኑን ተደራድረው የተስማሙበትን መንግሥቱን ለበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜ የሚያቆየውን ወጭም በፊርማቸው እንደሚያፀድቁ ተናግረዋል።

በበጀቱ ውስጥ ፕሬዚዳንቱ የጠየቁት የ5.7 ቢሊየን ዶላር የወሰን አጥር ግንባታ ወጭ ባይካተትም እንደራሴዎች በደረሱበት ስምምነት መሠረት የ1.4 ቢሊየን ዶላር ወጭ ለወሰን ደኅንነት ማጠናከሪያ እንዲውልና ለከፊል አጥር ሥራ ወጭ እንዲደረግ ተወስኗል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG