በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካና ብረት


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ሰሞኑን በመደዳ የተኩስ ጥቃቶች 31 ሰው የተገደለባቸውን የማዕከላዊ ምዕራቧን ኦሃዮ ከተማ ዴይተንና የደቡቧን ቴክሳስ ግዛት ኤል-ፓሶን ዛሬ፣ ነኀሴ 1/2011 ዓ.ም. እየጎበኙ ናቸው።

ጥቃቶቹ በሁለቱም ከተሞች ውስጥ የተከፈቱት ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ የጊዜ ልዩነት ውስጥ ነው። ዴይተን ላይ የገዳዩን የራሱን እህት ጨምሮ ዘጠኝ ሰው ተገደለ። ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰነው ኤል-ፓሶ ደግሞ በሌላ አደጋ ጣይ 22 ሰው ተገደለ።

ፕሬዚዳንት ትረምፕ ሁለቱንም ከተሞች እየጎበኙ ያሉት በነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ሽያጭና ዝውውር ላይ የጠበቀ ቁጥጥር እንዲደረግ አሜሪካዊያን አበርትተው እየወተወቱ ባሉበት ጊዜ ነው። ፕሬዚዳንቱ እራሣቸውም የመግቢያና የመኖሪያ ፍቃድ በሌላቸው ፍልሰተኞችና ስደተኞች ላይ የሚያወርዷቸው ዘለፋ አዘል ንግግሮችም ከብዙዎች ውግዘትና ቁጣን እያስከተሉባቸውም ነው።

ዋይት ሃውስ ደጅ ላይ ትናንት የወጡ በመሣሪያ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚፈልጉ ተሟጋቾች በዴሞክራቶች የበላይነት የተሞላው የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መምሪያ ቀደም ሲል ያፀደቀውን የሕግ ረቂቅ በሪፐብሊካን አብላጫ መቀመጫ የተያዘው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንዲያፀድቀው ሲጠይቁ ውለዋል።

የተወካዮች ምክር ቤቱ የሕግ ረቂቅ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ከጠብመንጃ ማሳያ ትርዒቶችና ከኢንተርኔት የሚሸምቱትን ጨምሮ ከመግዛታቸው በፊት በሁሉም ላይ የማንነትና የዳራቸው ፍተሻና ጥናት እንዲደረግ የሚያስገድድ የድንጋጌ ሃሣብ የያዘ ነው።

ፕሬዚዳንት ትረምፕ በሁለቱ ከተሞች ላይ የደረሰውን አስደንጋጭና አሳዛኝ አደጋ አስመልክተው ከትናንት በስተያ ሰኞ ንግግር ሲያደርጉ ብረት በማንም እጅ በዘፈቀደ ለመገኘቱ ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ ለእንዲህ ዓይነት የጭፍጨፋ አድራጎቶች ምክንያት ብለው በአፅንዖት የጠቀሱት የአዕምሮ ጤና መታወክን እና ሁከት የበዛባቸውን የቪድዮ ጨዋታዎችን ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንቱ ችግሩን ከአዕምሮ ጤና ጋር ማያያዛቸውን የአሜሪካ የሥነ-ልቦና ማኅበር ዛሬ አጥብቆ አውግዟል።

የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች እራሳቸው የእንደዚህ ዓይነት ሁከቶች ቀዳሚ ተጋላጭና ተጎጂዎች መሆናቸውን ማኅበሩ አስታውቆ የፕሬዚዳንቱ ንግግሮች ሕሙማኑ ሊያገኙ የሚገባቸውን ትኩረትና ሕክምና እንዳያገኙ፣ በየማኅበረሰባቸው ውስጥ ለመገለልና ለተጨማሪ ጥቃት እንዲዳረጉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ነው” ብሏል።

ለሙሉው ዘገባ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

አሜሪካና ብረት
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:58 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG