ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ የፍሎሪዳ የቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩትን ፓም ቦንዲን ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ አጭተዋቸዋል፡፡
የቀድሞው የምክር ቤት አባል ሪፐብሊካኑ ማት ጌትስ ራሳቸውን ከዕጩነቱ ማግለላቸውን ትላንት ሐሙስ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ትረምፕ ዐዲስ ዕጯቸውን አቅርበዋል።
ቦንዲ የትረምፕ የረዥም ጊዜ አጋር ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ሳሉ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ በቀረባበቸው ክስ ከቆሙላቸው ጠበቆች መካከል አንዷ እንደነበሩ አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ቦንዲ በቀድሞ የትረምፕ አስተዳደር ባልደረቦች የተቋቋመው የአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲ ተቋም ሊቀመንበር መኾናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የፊተኛው ዕጩ ጌትስ ከጾታዊ ምግባረ ብልሹነት እና ሱስ አስያዥ እፅ በድብቅ ከመጠቀም ጋራ የተያያዘ ክስ ከቀረበባቸው በኋላ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ሹመታቸው ሊጸድቅ አይችልም የሚል ጥርጣሬ የነበረ ሲሆን ጌትስ ትላንት በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “የኔ እጩነት የፕሬዝዳንት ትረምፕ እና ቫንስ ሽግግርን ወሳኝ የሥራ ትኩረት የሚከፋፍል እየሆነ መምጣቱ ግልጽ ነው” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም