ዋሺንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ ለሳምንታት በተቃውሞ እንቅስቃሴ መክረሟን ተከትሎ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደራቸው ለውህዳን የሕብረተሰብ ክፍሎች የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጠንክሮ ይሰራል በጤና ጥበቃም ረገድ ያሉበትን ልዩነቶች ይጋፈጣል ሲሉ ቃል ገቡ።
ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ የፕሬዚደንቱ ቃል ለማኅበረሰቡቹ ደኅንነት ዕድሎችና ክብር ለመገንባት የተዘጋጀ ባለ አራት ነጥብ ዕቅድ መሆኑን አመልክቷል።
ፕሬዚደንቱ ትናንት ሃሙስ ቴክሳስ ዳላስ ከተማ ላይ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተካሄደ የዘር ጉዳይና የፖሊስ አሰራር በተመለከተ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር የዚህ ዕቅዳቸው አንዱ አካል ኃይል አጠቃቀምን በሚመለከት ፖሊሶች ያለውን ከፍተኛውን ሙያዊ መስፈርት እንዲያሟሉ የሚጠይቀው አስፈጻሚ ትዕዛዛቸው እንደሚሆን ገልጸዋል።
አፍሪካውያን አሜሪካውያንና የፖሊስ አሰራን በሚመለከት ትረምፕ ይፋ ያደረጉት ዕቅድ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ ህይወቱ ማለፉ ያስቆጣቸውን የሚያረካ አይመስልም።