በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ በፔንስልቬንያ የድምጽ ቆጠራው ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ግጭት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ከዛሬው ምርጫ በፊት ባደረጉት፣ የመጨረሻ የምርጫ ዘመቻ፣ በፔንስልቬንያ ክፍለ-ግዛት፣ የተራዘመ የድምጽ ቆጠራ እንዲካሄድ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መፍቀዱ፣ የድህረ-ምርጫ ግጭት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የድምጽ መለኪያ አሃዞች እንደሚያሳዩት፣ በፔንስልቬያ ክፍለ-ግዛት፣ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በጥቂትም ቢሆን ትረምፕን እየቀደሙ ነው። በክፍለ-ግዛቲቱ በፖስታ ቤት በኩል የተሰጠውን ድምጽ ለመቁጠር፣ ከምርጫው በኋላም ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ተገምቷል። በፖስታ ቤት በኩል መመረጡ፣ ዲሞክራቶችን ሊጠቅም እንደሚችል ተገልጿል።

“የምርጫ ድምጽ ቆጠራ ጊዜ እንዲራዘም መፍቀድ፣ ለማጭበርበር ተግባር ሊያመች ይችላል። የህግ ስርዓታችንንም ይጎዳል። በመንገዶች ላይም ግጭት ሊያስነሳ ይችላል። ስለሆነም አንድ ነገር መደረግ አለበት” ሲሉ፣ ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ትረምፕ በመንገዶች ላይ ግጭት ሊነሳ ይችላል ስላሉት ጉዳይ፣ ዲሞክራቱ ተወዳዳሪያቸው ባይደን በጋዜጠኞች ሲጠየቁ፣

“ትረምፕ ለሚሉት ማንኛውም ነገር ምላሽ የመስጠት ፍላጎት የለኝም። ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድና ብዙ ስዎች ወጥጠው እንዲመርጡ ነው የምፍለገው” ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የምርመራ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ክሪስቶፈር ወይ፣ ባለፈው መስከረም ወር፣ የምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፖስታ ቤት በኩልም ሆነ፣ በአካል ተገኝቶ በሚደረገው ምርጫ፣ ማንኛውም አይነት የተቀነባበረ ምርጫን የማጭበርበር ተግባር አልታየም” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

XS
SM
MD
LG