በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ ልዩ መርማሪውን ያባርሩ ይሆን?


ራበርት መለር
ራበርት መለር

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የግል ጠበቃ ቢሮ እንዲበረበር የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥተው ዋራንቱን ተፈፃሚ ባደረጉት ልዩ መርማሪ ራበርት መለር እርምጃ ፕሬዚዳንቱ በብርቱ ቢቆጡም የማባረር ሃሣብ እስካሁን አለማንፀባረቃቸው እየተነገረ ነው።

በጠበቃቸው ማይክል ኮኸን ቢሮ ላይ የተካሄደውን ልዩ መርማሪ መለር የደገፉትን ድንገተኛ ብርበራ “አሣፋሪ ሁኔታ፣ በሃገራችን ላይ የተፈፀመ ጥቃት፣ የፍትሕ መጥፋት አዲስ ደረጃ” ሲሉ የውግዘት ውርጂብኝ አሰምተዋል ፕሬዚዳንት ትረምፕ።

“ለምንድነው ብድግ ብዬ መለርን የማላባርረው? አሣፋሪ ነገር ነው እየተካሄደ ያለው። ምን እንደሚመጣ እናያለን። እየተፈፀመ ያለውን ነገር ስታስተውሉት አሣዛኝ ሁኔታ ነው። እናም ብዙ ሰው ለምን አታባርረውም ይለኛል፤ በዚያ ላይ እንዳችም ያገኙት ነገር የለም” ብለዋል ለምንም ግምት ክፍት በሆነ አነጋገር።

ምርመራው እንደቀጠለ ነው። ባለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ውስጥ ሩሲያ ጣልቃ ገብ ጥቃት ፈፅማለች ተብሎ ከቀረበው ውንጀላ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክቶ ልዩ መርማሪው ራበርት መለር ስለ ትረምፕ ትንፍሽ ያሉት አንዳች ቃል አስከአሁን የለም።

በትረምፕ ነገረፈጅ ቢሮ ላይ ትናንት የተካሄደውን ብርበራ ጉዳይ በቅርብ 'አውቃለሁ' የሚል ምንጭ እንዳለው ተናግሮ ትናንት ምሽት ላይ አዲስ ዘገባ ያወጣው ዘ ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ሚስተር ኮኸን (ጠበቃው) በባንክ ላይ ከተፈፀመ ማጭበርበር፣ የገንዘብ ሽግግር ማጭበርበርና የምርጫ ዘመቻ ገንዘብ አያያዝ ደንብ ጥሰት ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አመልክቷል።

ስቶርሚ ዳንየልስ በሚል የመድረክ ስሟ ለምትታወቀው ሚስተር ትረምፕ 'ተኝተዋታል' ለተባለች አንዲት የሥጋዌ ቅብጠት ፊልም ተዋናዪት በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ባለፈው 2009 ዓ.ም ከተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምፅ ቀን ጥቂት ቀደም ብሎ እኒህ ትናንት የተበረበሩት ነገረፈጃቸው 130 ሺህ ዶላር 'አፍ መዝጊያ' እንደከፈሏት ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ስለዚያ ክፍያ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ትረምፕ በቅርቡ ተናግረዋል። በጋዜጠኛና በሚስተር ትረምፕ መካከል ሰሞኑን ተካሂዶ በነበረ አንድ አጭር ምልልስ “ማይክል ጠበቃዬ ነው፤ ለምን እንደከፈላት እራሱን ጠይቁት” ብለዋል።

የዚያ ክፍያ ለስቶርሚ ዳንየልስ መፈፀም ምናልባት የዶናልድ ትረምፕን የመመረጥ ዕድል ሊያጨልም ይችል የነበረ አጋጣሚን ለማለባበስ የተደረገ 'ሕገወጥ የምርጫ መዋጮ ነው' የሚል ዕምነት ያላቸው ሕግ አዋቅች አሉ።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ትረምፕ ልዩ መርማሪውን ያባርሩ ይሆን?
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:06 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG