በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለቱ የትረምፕ ክሦች


ሁለቱ የትረምፕ ክሦች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:45 0:00

ሁለቱ የትረምፕ ክሦች

ትላንት ማክሰኞ፣ በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሣቸውን ያደመጡት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ጥፋተኛ አለመኾናቸውን ከገለጹም በኋላ፣ እንቢተኝነት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።

በፕሬዚዳንታዊ እጩ ፉክክሩ፣ የሪፐብሊካኑን ፓርቲ ከፊት ኾነው በመምራት ላይ ያሉት ትረምፕ፣ በ37 የፌዴራል ወንጀሎች ተከሠዋል። የመንግሥትን ምሥጢር የያዙ ሰነዶችን ባልተገባ ኹኔታ በግል መኖሪያቸው ማቆየት፣ የሕግ ሒደትን ማደናቀፍ፣ ሤራ እና በሐሰት በመመስከር የሚሉ ክሦች ይገኙበታል።

ትረምፕ፣ የፍርድ ቤት ግቢውን ለቀው ከወጡ በኋላ፣ በፍሎሪዳ ግዛት ማያሚ ከተማ በሚገኝ በአንድ ተወዳጅ የኩባውያን ምግብ ቤት ጎራ ብለው፣ ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ አቅርበዋል። በሥፍራው ለነበሩ ሁሉ ምግብ አዝዘዋል፡፡ በኋላም፣ ኒው ጀርሲ በሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

“በአገራችን ታሪክ፣ እጅግ ሰይጣናዊ እና አደገኛ በኾነ ኹኔታ፣ ሥልጣን ያለአገባብ ጥቅም ላይ ሲውል ታዝበናል። እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። በሥልጣን ላይ የተቀመጠ ብልሹ ፕሬዚዳንት፣ የፖለቲካ ባላንጣውን በሐሰት ወንጀል አስይዟል፤” ብለዋል ትረምፕ፡፡

በፍሎሪዳው ፍርድ ቤት፣ በመቶ የሚቆጠሩ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች ተገኝተው ነበር። ትረምፕ፣ ከኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት ሲለቁ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ምሥጢራዊ የመንግሥት ሰነዶችን፣ ባልተገባ ኹኔታ በግል መኖሪያቸው አቆይተዋል፤ የሚል ክሥ ተመሥርቶባቸዋል። አንዳንዶቹ ሰነዶች፣ የአሜሪካን የኑክሌር እና የመከላከያ ምሥጢሮች የያዙ ናቸው። የስለላ ሕጉን በመጣስ፣ “የአገሪቱን የመከላከያ ምሥጢራዊ ሰነዶችን ኾን ብለው መውሰዳቸውን” የሚያመለክቱና የሕግ ሒደቱን ማደናቀፍ የሚሉ 31 የክሥ አንቀጾችን ጨምሮ 37 የወንጀል ክሦች ቀርበውባቸዋል።

የፌዴራል ምርመራ ቢሮው፣ ባለፈው ነሐሴ፣ በፍሎሪዳ ማያሚ በሚገኘውና ማር አ ላጎ በተሰኘው የትረምፕ ቅንጡ መኖሪያ ቤት ጎራ ብሎ ዶሴዎቹን ወስዷል። የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ልዩ አማካሪ የኾኑትና የትረምፕን ምርመራ የሚመሩት ጃክ ስሚዝ፣ “አገራችን ለሕግ የበላይነት ያላት ቁርጠኝነት ለዓለም ምሳሌ

ነው። እዚኽ አገር ያለው ሕግ፣ በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ ነው፤” ብለዋል። ጃክ ስሚዝ፣ የፍርድ ቤት ሒደቱ እንዲፋጠን ይሻሉ፤ ነገር ግን ጉዳዩን ለመጀመር እንኳ ወራት ሊፈጅ ይችላል፤ ተብሏል።

ትረምፕ፣ በመጪው ዓመት በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። ከሪፐብሊካን ፓርቲው እጩዎች ከፊት መሥመር ላይ ይገኛሉ።

አሁን እየታየ ያለው የክሥ ሒደት፣ ትረምፕ፥ የሪፐብሊካን ፓርቲን ለመወከል በሚወዳደሩበት ጊዜ፣ ተጽእኖ የሚያሳድር አይመስለኝም። ፓርቲውን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ከኾነ ግን፣ ከግል ተወዳዳሪዎች አንጻር ሲታይ ሊጎዳቸው ይችላል፤”

ኢፕሶስ የተሰኘው ተቋም እና ኤቢሲ ቴሌቪዥን ባደረጉት ዳሰሳ፣ አሜሪካኖች፥ ባለፈው መጋቢት፣ በትረምፕ ላይ ከቀረበውና “የወሲብ ፊልም ተዋናዪቱን ዝም ለማሰኘት መደለያ ከፍለዋል፤” ከሚለው ክሥ ይልቅ፣ የአሁኑ ክሥ ከበድ ይላል ብለው ቢያምኑም፣ ትረምፕ በወንጀል መከሰሰስ አለባቸው፤ በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ለሁለት ተከፍለዋል።

“አሁን እየታየ ያለው የክሥ ሒደት፣ ትረምፕ፥ የሪፐብሊካን ፓርቲን ለመወከል በሚወዳደሩበት ጊዜ፣ ተጽእኖ የሚያሳድር አይመስለኝም። ፓርቲውን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ከኾነ ግን፣ ከግል ተወዳዳሪዎች አንጻር ሲታይ ሊጎዳቸው ይችላል፤” ብለዋል፣ የኢፕሶስ ቃል አቀባይ ክሪስ ጃክሰን።

የኢፕሶስ ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ 47 በመቶ የሚኾኑ አሜሪካውያን፣ በትረምፕ ላይ የቀረበው ክሥ፣ “ፖለቲካዊ ነው፤” ብለው ያምናሉ። የትረምፕ ደጋፊ የኾኑትና በሰልፉ የተሳተፉት ግሬግ ዶናቫን፣ “በሕግ ላይ መሣለቅ እና የማይታመን ነው፤” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

እያንዳንዱ ክሥ፣ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ፣ ሕግ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው። በቀድሞም ይኹን በተቀማጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ላይ፣ ፌዴራል ክሥ ሲከፈት፣ ትረምፕ የመጀመሪያው ሲኾኑ፣ የዛሬው፣ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዳኛ ፊት የሚቀርቡበት ሁለተኛ ክሥ መኾኑ ነው።

የትረምፕ ሌላው ክሥ፣ ባለፈው ወር፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት፣ በጾታዊ ጥቃት እና ስም በማጥፋት በመክሠሥ፣ አምስት ሚሊዮን ዶላር የተፈረደላት የኒው ዮርክ ነዋሪት እና ጸሐፊ ጂን ካሮል፣ ተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ዶላር ክሥ ማቅረብ ትችላለች፤ ሲሉ፣ አንድ የአሜሪካ የፌዴራል ዳኛ ፈቅደዋል።

ዳኛው ሉዊስ ካፕላን ለከሣሿ የፈረዱት፣ ትረምፕ፣ “ግለሰቧን አስገድጄ ስላልደፈርኹ፣ ክሡ ውድቅ መደረግ አለበት፤” ብለው ከተከራከሩ በኋላ ነው። ትረምፕ ግለሰቧን “ቀውስ” ሲሉ ይጠሯታል።

ክሡ የተመሠረተው፣ እ.አ.አ. በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ፣ ትረምፕ ጂን ካሮልን፣ በኒው ዮርክ ማንሃታን አንድ የልብስ መሸጫ ሱቅ በሚገኝ የልብስ ልኬታ መሞከሪያ ክፍል ውስጥ አስገድደው ደፍረዋል፤ በሚል ነበር። ከሣሿ ባለፈው ወር፣ አምስት ሚሊዮን ዶላር ተፈርዶላታል።

ዳኛው በተጨማሪም፣ የአሜሪካው የፍትሕ መሥሪያ ቤት፣ ትረምፕን ተክቶ የተከሣሽ ሣጥን ውስጥ ይቆም እንደኹ ለማወቅ፣ የአንድ ወር ጊዜ ሰጥተዋል። የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ በቦታቸው የሚተካ ከኾነ፣ የ10 ሚሊዮን ብር ክሡ ውድቅ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም፣ መንግሥትን በስም ማጥፋት መክሠሥ ስለማይቻል። ትረምፕ ያን አጥብቀው ይፈልጉታል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ፣ ከዚኽ በፊት ትረምፕን ተክቶ መሟገት እንደሚችል ቢገልጽም፣ አሁን ግን፣ “ዐዲስ ክሥተቶች ታይተዋል” በሚል ጉዳዩን እንደገና ለማጤን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG