በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ በ2024 እንደሚወዳደሩ አስታወቁ


የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በ2017 ዓ.ም (የዛሬ ሁለት ዓመት) በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ መሆን እንደሚፈልጉ ትናንት፤ ማክሰኞ ምሽት ይፋ አደረጉ።

ፍሎሪዳ በሚገኘው የማር አ-ላጎ መኖሪያቸው አዳራሽ ለተጋበዙ እንግዶች አንድ ሰዓት ያህል በዘለቀ ንግግራቸው እርሳቸውን የተኩት የጆ ባይደን አስተዳደር “የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት አቆርቁዟል፤ ከተሞችን የወንጀልና የደም ገንዳ አድርጓል” ሲሉ ነቅፈዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውንና የተሸነፉበትን ምርጫ ውጤት እስካሁን ያልተቀበሉትና በሃገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ህንፃ ላይ ለተፈፀመው ህይወት የጠፋበት ሁከት ብዙዎች በተጠያቂነት የሚወቅሷቸው ትረምፕ “አሜሪካን እንደገና ታላቅና ገናና ለማድረግ ዛሬ ማታ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንትነት ዕጩ መሆኔን አስታውቃለሁ” ብለዋል።

ትራምፕ የፓርቲያቸው ዕጩ ሆነው ለመቅረብ ከስድስት ዓመት በፊት ከነበረውና እርሳቸው ከተመረጡበት ምርጫ የጠነከረ ፉክክር ሊጠብቃቸው እንደሚችል እየተሰማ ነው።

በዕጩነት ከሚጠበቁት መካከል የፍሎሪዳው አገረ ገዥ ሮን ደሳንቲስ የትረምፕ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የነበሩት ማይክ ፖምፔዪ እንደሚገኙበት ተመልክቷል።

በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ተከታታይ ያልሆኑ ሁለት የአገልግሎት ዘመን የነበራቸው ፕሬዚዳንት አንድ ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሳቸውም እአአ ከ1885 እስከ 1893 ያገለገሉት ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ እንደነበሩ ይታወቃል።

XS
SM
MD
LG