በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
የትረምፕ አስተዳደር ሥራቸውን ለሚለቁ የመንግሥት ሠራተኞች ጉርሻ እንደሚሰጥ አስታወቀ

የትረምፕ አስተዳደር ሥራቸውን ለሚለቁ የመንግሥት ሠራተኞች ጉርሻ እንደሚሰጥ አስታወቀ


ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ

አዲሱ የዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር፣ ፍላጎት ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በመጪው መስከረም መጨረሻ ሥራቸውን በፈቃዳቸው የሚለቁ ከሆነ የስምንት ወር ደመወዝ ጉርሻ እንደሚሰጥ ትላንት ለመንግሥት ሠራተኞች በላከው ኢሜይል አስታውቋል።

ፕሮግራሙ የዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንና ሠራተኞችን ለመቀነስ የያዘው ዕቅድ አካል መሆኑ ተመልክቷል።

ሠራተኞች ፍላጎታቸውን እስከ መጪው ሐሙስ ማለትም እአአ የካቲት 6 ቀን ድረስ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተመልክቷል። ይህን የሚያደርጉ ሠራተኞች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ሙሉ ለሙሉ ከቢሮ እንዲሠሩ የሚያዘው ደንብ ላይመለከታቸው እንደሚችልም ታውቋል።

በስደተኞችና በብሔራዊ ፀጥታ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ እንዲሁም የፖስታ ቤት ሠራተኞች ፕሮግራሙ እንደማይመለከታቸውም ተመልክቷል።

የመንግሥት ሠራተኞችን የሚወክሉ የሠራተኛ ማኅበራት የአስተዳደሩን ሐሳብ ተቃውመዋል። ሠራተኞች እንዳይስማሙም መክረዋል።

“የፌዴራል ሠራተኞች ታማኝ፣ አስተማማኝና በየቀኑ ለመሻሻል የሚጥሩ መሆን አለባቸው” ብሏል ከአስተዳደሩ የተላከው መልዕክት፡፡

የቪኦኤ ሠራተኞችን ጭምር የሚወክለው የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ፌዴሬሽን ኃላፊ ኤቨረት ኬሊ፣ "ሠራተኞች አዲሱ ፕሮግራም በፈቃደኝነት የሚያደርጉት ጉዳይ አድርገው እንዳያዩት" አሳስበዋል። አክለውም ፣"የአስተዳደሩ ተግባር የሚያሳየው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ጤናማ ያልሆነ አካባቢን መፍጠርና ሠራተኞች መቆየት ቢሹ እንኳ ሥራቸውን መቀጠል እንዳይችሉ ለማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG