ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከእርሣቸው የቀደሙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ “በምርጫው ወቅት ኒው ዮርክ በሚገኘው ሕንፃዬ ላይ የስልክ መሥመሮቼን ጠልፈው ይሰልሉኝ ነበር” ሲሉ ላሰሙት ክሥ ዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት ማስረጃ እንዲያቀርብ ግፊቱ አሁንም እንደበረታ ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ሚኒስቴር ማስረጃዎቹን ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ለተወካዮች ምክር ቤቱ የመረጃ ወይም የስለላ ጉዳዮች ኮሚቴ ጥያቄ አስገብቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ትረምፕ ላሰሙት ክሥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ተሰጥቶት የነበረው የጊዜ ገደብ ትናንት ሲያልቅ ነው ይህንን የማራዘሚያ ጥያቄ ያስገባው፡፡
ብዙዎች “ምንኛ ደፋር ክሥ ነው!” እያሉት ነው ይህንን ሚስተር ትረምፕ በትዊተር ያሠራጩትን አቤቱታቸውን፡፡ “ያስደነግጣል፤ ማሸነፌ ከመበሰሩ በፊት ኦባማ ትረምፕ ሕንፃ ላይ ስልኮቼን ጠልፎ ሲሰልለኝ እንደነበር አሁን አወቅሁ፡፡ ግን ምንም አላገኘም፡፡” ነበር የሚለው የትዊተር መልዕክታቸው፡፡
ይህ የትረምፕ አቤቱታ መልዕክት ከወጣ ከአንድ ሣምንት ጥቂት ዘለግ ያለ ጊዜ አለፈ፡፡ ኦባማ በትረምፕ መኖሪያ ቤትም ሆነ ቢሮዎች ላይ ያደረጉት ምንም ዓይነት ማነፍነፍ መኖሩን የሚያረጋግጥ አንዳችም ማስረጃ አልቀረበም፡፡
በሌላ በኩል ግን ይህ ትረምፕ ክሥ ያሰሙበትን ዓይነት አድራጎት “ጨርሶ አልተፈፀመም” ሲሉ በኦባማ አስተዳደር የብሔራዊው የሥለላ ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ጄምስ ክላፐር ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
“በስለላው ማኅበረሰብ የትኛውም አካል በምርጫ ዘመቻው ወቅት በትረምፕ ሕንፃ ላይ የተካሄደ አንዳችም የስልክ መሥመር ጠለፋና ሥለላ ሥራ አልነበረም” ብለዋል ክላፐር፡፡
የትረምፕ አስተዳደር ሰዎች ግን ምንም ማስረጃ ባያቀርቡም ፕሬዚዳንቱ ያሰሙት ክሥ “ትክክል ነው” እያሉ ስሞታውን ማጠናከራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ትረምፕ ከፍተኛ አማካሪ ኬሊአን ኮንዌይ አንዷ ናቸው፡፡ “ማስረጃ የለኝም፤ ሆኖም ግን ለዚህም ነው በተወካዮች ምክር ቤቱ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ ያለው” ብለዋል፡፡
የዋይት ሃውሱ የፕሬስ ኃላፊ ሾን ስፓይሰር ሰኞ፣ መጋቢት 4/2009 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ጋር ሲነጋገሩ ነገሩን ጥቂት ጠምዘዝ አድርገው “ምናልባት ያ ስለላ የተካሄደው በሥልክ ጠለፋም ላይሆን ይችላል” ብለዋል፡፡ ‘ስለላ ተካሂዷል’ የሚለውን መሠረታዊ ክሥ ግን አልሠረዙም፡፡
“ትረምፕ የሚያስቡት ‘ፕሬዚዳንት ኦባማ እራሣቸው ኒው ዮርክ ወርደው ስልኬን ጠለፉብኝ’ ብለው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ … እ … እኔ እንደማስበው በ2016ቱ /እአአ/ ምርጫ ወቅት በኦባማ አስተዳደር የተከናወኑ የስለላና ሌሎችም አድራጎቶች ስለመኖራቸው ጥያቄ የለውም” ብለዋል፡፡
ይህንን ጉዳይ የሚመለከተው የተወካዮች ምክር ቤቱ የመረጃና የሥለላ ጉዳዮች ኮሚቴ ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ሂደት ውስጥ እጆቿን አስገብታ እንደሆነም እየፈተሸ ነው፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ