በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አልተነሣም


አሜሪካዊያን ኤርትራ ውስጥ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንዲጠነቀቁ ቀደም ሲል ጥሎት የቆየውን ማስጠንቀቂያ አሁንም ማስቀጠሉን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታውቋል፡፡

በኤርትራ የድንበር አካባቢዎች ለመተንበይ የማይቻል የፀጥታ ሁኔታ በመኖሩና ባለሥልጣናቷም በሃገር ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመገደባቸው የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ወደ ኤርትራ መጓዝ ያለውን የአደጋ ሥጋቶች ማስጠንቀቂያ ማስቀጠሉን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዛሬ፣ ነኀሴ 26/2008 ዓ.ም ባወጣው ማስታወቂያ ገልጿል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት ሠራተኞች ጨምሮ ሁሉም የውጭ ዜጎች ከዋና ከተማዪቱ አሥመራ ውጭ ለመጓዝ ፍቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ይኸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ አስታውሷል፡፡

ይህ ሁኔታም የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ከአሥመራ ውጭ የቆንስላም ይሁን የአጣዳፊ ሁኔታ አገልግሎቶችን የመስጠት አቅሙን እንደሚገድበው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አመልክቷል፡፡

ይህ የዛሬው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሚያዝያ 6/2007 ዓ.ም ወጥቶ የነበረውን የሚተካ መሆኑም ተገልጿል፡፡

“ወደ ሁሉም የድንበር አካባቢዎች አትሂዱ” ይላል ማስጠንቀቂያው፡፡

ባለፈው ሰኔ 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ ዳንበር ላይ በተካሄደው ውጊያ ብዙ ሕይወት መጥፋቱ ሪፖርት መደረጉን የጠቆመው የዛሬው ማስጠንቀቂያ ከጎረቤቶቿ ከጅቡቲና ከኢትዮጵያ ጋር የቀጠለው የኤርትራ የፖለቲካና ወታደራዊ ፍጥጫ ግጭት ሊያገረሽ የመቻሉን ሥጋት እንደሚደቅን አሳስቧል፡፡

ባሉት የሥጋት ሁኔታዎች ምክንያትም ከሱዳን ጋር ወዳሉ የድንበር አካባቢዎችም ከመጓዝ መቆጠብ እንደሚያስፈልግ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መክሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው ማስጠንቀቅያ እዚህ ላይ ያንብቡ።

XS
SM
MD
LG