በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አዲሱ የጉዞ ዕገዳ - ድጋፍና ተቃውሞ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

ከአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ የጉዞ ዕገዳ ዝርዝር የተፋቀችው የኢራቅ መሪዎች አዲሱን የዕገዳ ትዕዛዝ ሲያሞካሹ፤ አሁንም በዝርዝሩ ውስጥ የቀረችው የሱዳን መሪዎች ግን ትዕዘዙን አውግዘውታል፡፡

ከአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ የጉዞ ዕገዳ ዝርዝር የተፋቀችው የኢራቅ መሪዎች አዲሱን የዕገዳ ትዕዛዝ ሲያሞካሹ፤ አሁንም በዝርዝሩ ውስጥ የቀረችው የሱዳን መሪዎች ግን ትዕዘዙን አውግዘውታል፡፡

የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ ጀማል ለአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና አውታር በሰጡት ቃል “የኢራቅ ከዕገዳው ዝርዝር መፋቅ የእሥላማዊ መንግሥት ቡድን ፅንፈኞችን ለመፋለም በኢራቅና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ትብብር ያጠናክረዋል” ብለዋል፡፡

ኢራቅ ከዕገዳው ዝርዝር እንድትወጣ የተደረገው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከኢራቅ መንግሥት ጋር በመሆን የተጓዦችን ማንነት ለማጣራት የሚደረገው ሥራ እየተጠናከረ መምጣቱን ከልሶ ከፈተሸ በኋላ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክ ቲለርሰን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከኢራን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊብያና ሶማሊያ ጋር ለመጭዎቹ ዘጠና ቀናት ለዜጎቻቸው ቪዛ እንዳይሰጥ በወጣው አዲስ ዕገዳው ዝርዝር ውስጥ የቀረችው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትራምፕ አዲስ ትዕዛዝ የተሰማውን ቅሬታ ተናግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትረምፕ አዲስ ትዕዛዝ ምንነት በግልፅ ተለይቶ እስኪታወቅ ድረስ ዜጎቹ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሊያደርጉ ያቀዱትን ጉዞ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ የናይጀሪያ መንግሥት ጥሪ አውጥቷል፡፡

በውጭ ጉዳይና ግዩራን ጉዳዮች የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት የሆኑት አቢኬ ዳዊሪ ኤሬዋ የመንግሥታቸው ማሳሰቢያ የወጣው “በቅርቡ ከዩናይትድ ስቴትስ አይሮፕላን ጣቢያዎች ሰዎች ወደየመጡበት እንዲመለሱ በመደረጋቸው ሰዉ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለመምከር ነው” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የተከለሰው የፕሬዚዳንት ትረምፕ የጉዞ ዕገዳ ትዕዛዝ ብዙ ቁጥር ያላቸው የዩናይትድ ስቴትስ ሪፐብሊካን እንደራሴዎች እንደሚደግፉት በአድናቆት ቢገልፁም የዴሞክራቲክ ፓርቲው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል በርኒ ሳንደርስና በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች “ዘረኛና ፀረ-ሙስሊም” ሲሉ አውግዘውታል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሪፐብሊካኑ ራያን ፖል አዲሱ ትዕዛዝ ዩናይትድ ስቴትስን ከአደጋ የመጠበቅን የጋራ ግባችንን ወደፊት ያራምዳል ሲሉ ያሞካሹት ሲሆን ሪፐብሊካኑ ሴናተር ሊንድዚ ግራሃም ደግሞ አዲሱ ዕገደ ካለፈው በተለየ ሁኔታ በሐይማኖት ላይ ያነጣጠረ ተደርጎ እንደማይወሰድና የሕግ ፍተሻዎችን ያልፋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ሕግ የሚመለከተው ደኅንነታቸውና ፀጥታቸው ጥያቄ ውስጥ ከወደቀና በጨነገፉ መንግሥታት የሚነሱ ግለሰቦችን ነው ብለው እንደሚያምኑ ግራሃም ተናግረዋል፡፡

አሮጌውና አዲሱ የጉዞ ዕገዳ
አሮጌውና አዲሱ የጉዞ ዕገዳ

ዴሞክራቱ በርኒ ሳንደርስ ግን ከሪፐብሊካን ባልደረቦቻቸው ሃሣብ ጋር በሚቃረን ሁኔታ “ትዕዛዙ ሙስሊሞችን ነጥሎ ለመጉዳትና ሊከፋፍለን የታሰበ ነው” ሲሉ በብርቱ እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሃያ ስምንት የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ስደተኞችን የሚያሰፍረውና በአርባ ሃገሮች ውስጥ የሚንቀሣቀሰው ዓለምአቀፍ አዳኝ ኮሚቴ የሚባለው ቡድን የጉዞ ፍተሻዎቻቸውን ጨርሰው ለመንቀሣቀስ እየጠበቁ ያሉ ወደ ስድሣ ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ በአዲሱ ትዕዛዝ ምክንያት አደጋ ላይ መውደቁን አስታውቋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ደግሞ አዲሱን ትዕዛዝ “በሌላ መጠቅለያ የቀረበ ያው የነበረው የጥላቻና የፍርሃት ጥቅል ነው” ብሎታል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG