የሕወሓት የቀድሞ ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋና አራት ሰዎች ተደብቀውበት ከነበረው ቦታ ተገኝተው መታሰራቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
የሕወሓት ነባር ታጋይ የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች አራት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የመከላከያ ሠራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብሪጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ጠቅሶ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገቧል። በተጨማሪም ወይዘሮ አልጋነሽ መለስ የተባሉ ግለሰብ ገደል ውስጥ ገብተውሕይወታቸው ማለፉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እያካሄደ እንደሆነ በሚገልፀው ሕግ የማስከበር ሂደትውስጥ ለሕግ ለማቅረብ የእስር ማዘዣ ቆርጦ እያፈላለጋቸው እንደሚገኝ ሲገልፅ ከቆየው የሕወሓት አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖች አንዱ የሆኑት የቀድሞው ነባር የሕወሓት ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ እና ሌሎች ግለሰቦችን “ለሰው ልጅ እጅግ አስቸጋሪ” ከሆነ ቦታ ላይ በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ብሪጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ አስታውቋል።
ከአቶ ስብሃት በተጨማሪ መንግሥት በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የገለፀው፤በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ውስጥ ሃኪም እንደነበሩ የተገለፀው ሌተና ኮሎኔል ፀአዱ ሪች፣ማዕረጋቸው የተገፈፈው ኮሎኔል ክንፈ ታደሰ እና ኮሎኔል የማነ ካህሳ እንዲሁም አቶ አስገደ ገ/ ክርስቶስበቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጀነራሉ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በዚሁ ዜና ላይ እንደተጠቀሰው የሜጀር ጀነራል ሃየሎም አርአያ ባለቤት የነበሩትና በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ እንደነበሩ የተገለፀው ወይዘሮ አልጋነሽ መለስ የተባሉ ግለሰብ የሕወሓት አመራሮችን ለመያዝ በነበረው ሂደት ውስጥ ለማምለጥ ሲሞክሩ “ገደል ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው አልፏል” ብለዋልብሪጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ።
የመከላከያ ሠራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብሪጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ በትላንትናው ዕለት አራት የሕወሓት አመራሮች መገደላቸውና ዘጠኝ መታሠራቸውን መግለፃቸው አይዘነጋም።