በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዶር. ደብረ ጽዮን የሚመራው ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሹሞች “አልቀበልም” አለ


ለሁለት ከተከፈለው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አመራር አንዱ የኾነው፣ በዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ቡድን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. የሾሟቸውን ሁለት የዞን አስተዳዳሪዎች እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ዐዲስ ዋና አስተዳዳሪዎችን የሾሙት፣ በምክትል አስተዳዳሪዎች ሲመሩ ለቆዩት ለሰሜናዊ ምዕራብ እና ለደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ ዞኖች ነው።

ሁለቱ ዐዲስ አስተዳዳሪዎች፥ ለደቡብ ትግራይ ዞን የተሾሙት አቶ ፀጋይ ገብረ ተኽለ እና ለሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ዞን የተሾሙት አቶ ተኽላይ ፍቓዱ ሲኾኑ፣ የቀድሞዎቹ የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ወይዘሮ ሊያ ካሳ እና አቶ ተኽላይ ገብረ መድኅን፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከተነሡ ከ10 ወራት በኋላ ነው በምትካቸው መሾማቸው የተገለጸው።

በአንጻሩ፣ በዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ጽሕፈት ቤት፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ነሓሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ደብዳቤ፣ “ሹመቱ ተቀባይነት የለውም” በማለት ተቃውሟል።

በዶር. ደብረ ጽዮን የሚመራው ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሹሞች “አልቀበልም” አለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:30 0:00

ሹመቱን እየሰጡ ያሉት፣ “በቅርቡ በተካሔደው የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ ህወሓትን ወክለው እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ናቸው፤” ሲል የገለጸው ደብዳቤው፣ የሚሾሙት ሰዎች ግን፣ በየወረዳው በሚገኙ የህወሓት የአስተዳደር ኮሚቴዎች ውስጥ፣ አባል ኾነው መሳተፍ እንደማይችሉ አስታውቋል።

ጽሕፈት ቤቱ፣ “በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚገኙ የተወሰኑ አመራሮች ለረዥም ጊዜ ህወሓትን የማፍረስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤” ሲል ከሷል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ ለሁሉም የህወሓት የዞንና የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች በላኩት በዚኹ ደብዳቤ፣ “የፓርቲውን አሠራር እና ሕጋዊ አካሔድ ባልተከተለ መንገድ እየተካሔደ ነው፤” ያለው የሥልጣን ሹም ሽር፣ “ህወሓትን ከሥሩ ለመንቀል እየተደረገ ያለ አሻጥር ነው፤” ሲል ከሷል፡፡ በዞንና በወረዳ የሚገኙ የህወሓት አመራሮችም፣ ከተሾሙት ጋራ እንዳይተባበሩ አሳስቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ከህወሓት ጽሕፈት ቤት ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የኾኑት የማነ ካሳ፣ ኹኔታው የመንግሥት እና የፓርቲ መደበላለቅ ሥር የሰደደ እንደነበር ማሳያ መኾኑን አመልክተዋል።

የህወሓት አመራሮች፣ ከፓርቲው ምዝገባ እና ሕጋዊ ሰውነት፣ እንዲሁም የድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅት ጋራ በተያያዘ ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ቆይተዋል።

ከእነዚኽ ሁለት ቡድኖች ውስጥ፣ በቅርቡ በመቐለ የሰማዕታት ሐወልት አዳራሽ ሲያካሒድ የሰነበተውን ጉባኤ ያጠናቀቀው፣ በዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ቡድን፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር የኾኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን፣ “ከኃላፊነት እና ከአመራር አባልነት አንሥቻለኹ፤” ብሏል።

ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን በድጋሚ የህወሓት ሊቀ መንበር አድርጎ መምረጡን፣ የጉባኤው ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ዐማኑኤል አሰፋ ደግሞ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን በመተካት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ኾነው መመረጣቸውንም ጉባኤው ማስታወቁ ይታወሳል።

የጉባኤው ዝግጅት፥ “የፓርቲውን ደንብ እና አሠራር የጣሰ ነው፤” ሲሉ መካሔዱን ሲቃወሙ የቆዩት እነአቶ ጌታቸው በአንጻሩ፣ “ተቃዋሚ የተባሉ አመራሮችን ለማስወገድ ያለመ” እንደኾነ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

የእነአቶ ጌታቸው ረዳ ቡድን፣ “ህወሓትን የማዳን” በሚል በጠራው ስብሰባም፣ በእነዶር. ደብረ ጽዮን ቡድን የተካሔደው ጉባኤ፣ “ሕጋዊ አይደለም፤ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም ሕጋዊ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፤” በማለት ውሳኔዎቹን ማጣጣሉ አይዘነጋም።

አቶ ጌታቸው፣ ባለፈው ነሓሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ለትግራይ ክልል የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች በጻፉት ደብዳቤ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሔድ የሚቻለው፣ “በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ዕውቅና ብቻ ነው፤” ሲሉ መመሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድም፣ “ሕጋዊ ሒደቱን አላሟላም” በሚል ዕውቅና የነፈገው የእነዶር. ደብረ ጽዮን ቡድን ያካሔደው ጉባኤ፣ ውሳኔዎቹም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ቀደም ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG