የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ዛሬ ረቡዕ ታኅሣስ 26/2015 ዓ.ም በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ "ማታለል እና ውሸቶች የህወሓት መለያዎች ናቸው” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
አቶ የማነ በትዊተራቸው ይህን ያሉት፣ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “በሰላም መንገድ ላይ የቆሙ አጥፊዎች” ባሏቸው አካላት ላይ “ቁጣችንን ማሳየት አለብን” ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ታኅሣስ 25/2015 ዓ.ም በጻፉት የትዊተር መልዕክት “ትክክለኛ አእምሮ ያላቸው ወይም በጤናማ መልኩ የሚያስቡ ሰዎች ሰላም የማስፈን አስፈላጊነትን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው የመመለስ፣ በሰላም መንገድ ላይ የቆሙትን አጥፊዎች እንዲታቀቡ ማድረግን፣ ለመቀበል አይቸገሩም” ብለዋል፡፡
“ነገሮች ወደ መደበኛነት እንዲመለሱ ለማረጋገጥ የሚደረጉ ተግባራት ሁሉ እንደ ነውር መቆጠር አልነበረባቸውም” ያሉት አቶ ጌታቸው “ከመረብ ማዶ ያለው አመራር ልዩነት እንዲፈጠር የሚለምን ይመስላል” ሲሉም አክለዋል።
በግልጽ ማንነታቸውን ባይጠቅሱም “በኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍል ያሉ አበረታች ደጋፊዎቻቸውም ለአምባገነኑ ትኩረት የሰጡ ይመስላሉ” ብለዋል። ለእንደዚህ ዓይነት ተግባር “ቁጣችንን ማሳየት አለብን፤… ሰላም ብቸኛው ጨዋታ ነው፤ ወይም እኛ የምናምነው ይሄን ነው” ሲሉም ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት፡፡
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፣ የአቶ ጌታቸውን የትዊተር መልእክት በቀጥታ ባይጠቅሱም “ለሁለት ዓመታት የትጥቅ ጦርነት ካደረገ በኋላ ህወሓት እንደተጠበቀው ዛሬ ‘የሰላም ሻምፒዮን’ መስሎ እየታየ ነው” ብለዋል። አቶ የማነ “የህወሓት አጭበርባሪ መሪዎች እና ደጋፊዎቹ ተጨማሪ አፀያፊ ውሸቶችን በማሰራጨት ላይ ናቸው” ሲሉም ወንጅለዋል።
ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሠላም ሥምምነት በተፈራረመው ህወሓት እና በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ያለው መወነጃጀል የቀጠለው የሥምምነቱ የትግበራ ሂደት በተሻለ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ እየተገለፀ ባለበት ወቅት ነው።