ኦሊቪያ ቾው፣ የካናዳ ዋና ከተማ - ቶሮንቶ፣ ከንቲባ ኾነው የተመረጡ፣ የመጀመሪያዪቱ ትውልደ ቻይናዊት ኾኑ።
የድምፅ አሰጣጥ ውጤቱ እንደሚያሳየው፣ ቾው፥ 37 በመቶ ድምፅ በማግኘት ሲያሸንፉ፣ ተፎካካሪያቸው የቀድሞ ምክትል ከንቲባ እና ባይሎዋ ደግሞ 32 ከመቶ ድምፅ አግኝተዋል።
ቾው፥ ትልቁን የካናዳ ከተማ እንዲመሩ የተመረጡ ሁለተኛዋ ሴት ሲኾኑ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር፣ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን በድጋሚ የተመረጡትን ጆን ቶሪን ይተካሉ፡፡
ቶሪን፥ ከተመረጡ ከአራት ወራት በኋላ፣ ከጋብቻ ውጪ ከሠራተኛቸው ጋራ ግንኙነት መፈጸማቸውን አምነው፣ ከሓላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ቾው ማሸነፋቸውን ተከትሎ፣ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ “በወደፊት ሕይወታችኹ እና አንዳችን ለሌላችን ምን መሥራት እንደምንችል ጥርጣሬ ካላችኹ፣ ይህ ምሽት ለእናንተ ምላሽ ነው፤” ብለዋል።
የ66 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ቾው፣ ከተወለዱበት ሆንግ ኮንግ ወደ ካናዳ የሔዱት፣ የ13 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር፡፡ ቀደም ሲል፣ የካናዳ ፓርላማ አባል እና የቶሮንቶ ከተማ ምክር ቤት አባል ኾነው አገልግለዋል።
ግራ ዘመም አቋም ያላቸው ቾው፣ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት፣ 2ነጥብ7 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባትና ቤት አልባነት እያደገ በሚገኝባት ቶሮንቶ፣ 25ሺሕ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ቃል ገብተዋል።