በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፍሪካዊያን ሯጮች በቶኪዮ ኦሎምፒክ


አትሌት ለሜቻ ግርማ
አትሌት ለሜቻ ግርማ

አፍሪካዊያን የሩጫው ዘርፍ ገናና መሆናቸውን ዳግም አሳይተዋል። ኢትዮጵያም በማህደሯ ላይ አንድ የብር እና አንድ የነሃስ ሜዳሊያዎችን አክላለች። በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር የሞሮኮው ሱፊያን ኤል ባካሊ ውድድሩን 8 ደቂቃ ከ8 ሰከንድ፣ ከ90 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስገኝቷል። ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና የኬንያው ቤንጃሚን ኪገን በሰከንዶች ልዩነት ተከታትለው በመግባት የብር እና ነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል።

ሌላው በጉጉት የተጠበቀው የሴቶች 5000 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ኔዘርላንድን በወከለችው ፣ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሲፋን ሀሰን አሸናፊነት ተጠናቋል። ሲፋን 12 ከግማሹን ዙር በ14 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ ኔዘርላንድን ለወርቅ አብቅታለች። ኬንያዊቷ ሄለን ኦብሪ የብር፣ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋዬ የነሃስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት የሀገራቸውን የሜዳሊያ ቁጥር ከፍ አድርገዋል። በኦሎምፒክ የክብር መዝገብ ላይም ስማቸውን አስመዝግበዋል፥

***

የቶኪዮ ኦሎምፒክ የሁለተኛ ሳምንት ክንውኖችን ጀምሯል። ቀልብ ሳቢ ስፖርታዊ ትዕይንቶችም እየታዩ ይገኛሉ። በከፍታ ዝላይ ዘርፍ የተወዳዳሩ አንድ ጣልያናዊ እና አንድ ኳታራዊ ተወዳዳሪ ሁለቱም የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሸለሙ ተወስኗል።

ጣልያናዊው ጂያንማርኮ ታምቢሪ እና ኳታራዊው ሙታዝ ባርሲም አሸናፊውን ለመለየት የተቀመጠውን የ2 ሜትር ከ39 ሳንቲሜትር ከፍታ በዝላይ ለማለፍ ሶስት ጊዜ ሞክረው አልተሳካላቸውም ነበር። በስተመጨረሻ ዳኞች ተወዳዳሪዎቹ ከተስማሙ ለሁለቱም የወርቅ ሜዳሊያ መስጠት እንደሚችሉ ነግረዋቸዋል። መስማማታቸውን ያስታወቁት ተወዳዳሪዎች በእምባ የታጀበ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይቷል።

በተያያዘ ዜና የቪንዚዌላ ሱሉስ ዝላይ ተወዳዳሪ የሆነችው ዩሊማር ሮጃስ ከ26 ዓመት ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን የኣለምም ሆነ የኦሎምፒክ ክብረወሰንን በአንድ ቀን አስመዝግባለች። ሮጃስ በመጨረሻ ሙከራዋ 15.67 ሜትር ለመዝለል ችላለች።

***

የቶኪዮ ኦሎምፒክ መልካም ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት መድረክም ሆኗል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት በወንዶች 800 ሜትር ሩጫ ተወዳዳሪ የሆኑት የዩናይትድ ስቴትሱ አይዜያ ጄዊት እና የቦትዋናው ኔጂል አሞስ ናቸው። ለሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ውድድራቸውን በሚያደርጉ ጊዜ ተጠላልፈው ቢወድቁም አንዳቸውን አንዳቸው ላይ ንዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ በወንድማማችነት መንፈስ በመተቃቀፍ ውድድሩን ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በ54 ሰከንንዶች ዘጝይተው ጨርሰውታል።ከውድድሩ በኃላ አሞስ ወደ መጨረሻው ዙር ውድድር እንዲገባ ሲፈቀድለት ጄዊት ግን ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

***

የቶኪዮ ኦሎምፒክ የውዝግብ አፍታዎችንም እያስተናገደ ነው። በግዳጅ ወደ ሀገሬ እንድሳፈር ልደረግ ነው ያለችው የቤላሩስ ተወዳዳሪ ክርስቲና ሲማኑስካያ ሀኔዳ በተሰኘው አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ከለላ አግኝታለች። ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ ለአትሌቷ ማናቸውንም ድጋፍ ለመስጠት ጥያቄ አቅርበዋል። የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ተወካዮችም እንዳነጋገሯት ተሰምቷል። አትሌቷ አሰልጣኟ በሌሊቱ ወደ ክፍሏ በመሄድ ውድድሯን በማቋረጥ ወደ ሀገሯ እንድትመለስ በበላይ አካል መታዘዙን መናገራቸውን እኣ በግዳች በቱርክ አየር መንገድ ሊያሳፍሯት መመከራቸውን ተናግራለች። ተጨማሪ ዘገባዎች የተገኙት ከአሶሼትድ ፕረስ ነው።

XS
SM
MD
LG