በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቲም ዋልዝ እጩነታቸውን በይፋ ተቀበሉ


የሜንሶታ አገረ ገዥ ቲም ዋልዝ
የሜንሶታ አገረ ገዥ ቲም ዋልዝ

የሜንሶታው አገረ ገዥ ቲም ዋልዝ የዲሞክራቲክ ፓርቲውን በመወከል ለምክትል ፕሬዝደንትነት እንዲወዳደሩ መታጨታቸውን እንደተቀበሉ ረቡዕ ምሽት ቺካጎ ላይ በቀጠለው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ አስታውቀዋል።

“ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንትነት እንደወዳደር በእጩነት መምረጣችሁን ስቀበል በሕይወቴ ትልቅ ክብር ይሰማኛል” ብለዋል ቲም ዋልዝ።

“በእኔ ላይ እምነት በመጣላችሁ አመሰግናለሁ” ብለዋል ቲም ዋልዝ። በእጩነት ያቀርቧቸውንና ፕሬዝደንታዊ እጩ የሆኑትን ካመላ ሄሪስንም አመስግነዋል።

የካመላ ሄሪስ አስተዳደር ታክስን እንደሚቀንስ፣ አሜሪካውያን ቤት እንዲገዙ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር፣ የመድሃኒት ዋጋንም ተመጣጣኝ ለማድረግ ከኩባንያዎች ጋራ እንደሚደራደር ተናረዋል።

“ካመላ ሄሪስ ጠንካራ ነች፣ ካመላ ሄሪስ ልምድ አላት፣ ካመላ ሄሪስ ዝግጁ ነች” ብለዋል ዋልዝ።

የ60 ዓመቱ ዋልዝ ሃገረ ገዥ ከመሆናቸው ቀደም ብሎ፣ በርካታ ስደተኞች የሚኖሩበትን የሜንስቶ ግዛትን በመወከል የአሜሪካ ምክር ቤት ዓባል ነበሩ። በግዛቲቱ ከሚኖሩ ስደተኞች መካከል ከኢትዮጵያና ሱማሊያ የመጡ ይገኙበታል።

በዲምክራቶቹ ጉባኤ ላይ የቀድሞ ፕሬዝደንት ድናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች በጥር 6 ቀን 2021 (እ.አ.አ) የአሜሪካ ካፒቶል ላይ ጥቃት መክፈታቸውን በማስታወስ ሲያወግዝ አምሽቷል።

“ጥር 6 ቀን ለዲሞክራሲያችን አደገኛ ወቅት ነበር” ብለዋል የቀድሞ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ።

የቀድሞ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ
የቀድሞ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ

“በዲሞክራሲያችን ላይ ማን ጥቃት እንደሰነዘረ አንርሳ” ብለዋል ፐሎሲ ትረምፕን ለማመልከት በሚመስል አነጋገር።

በምሽቱ ሌላው ተናጋሪ የቀድሞው ፕሬዝደንት የነበሩት ቢል ክሊንተን ነበሩ።

በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ጆ ባይደን ለሰጡት አመራር ያመሰገኑት ክሊንተን፣ “የታመሙትን አዳኑ፣ ሌሎቻችንንም ወደ ሥራ እንድንመለስ አደረጉ” ብለዋል።

“ለዩክሬን ቆመዋል። በመካከለኛው ምሥራቅም ተኩስ አቁም እንዲደረግ እየሞከሩ ነው” ሲሉ አክለዋል ክሊንተን።

ባይደን ችቦውን ለካመላ ሄሪስ ማስተላለፋቸውንም ክሊንተን አድንቀዋል። ካመላ ሄሪስ የሁሉንም መብት እንዲጠበቅ እንደሚያደርጉም አውስተዋል።

ዲሞክራቶች በጣም ተማምነው ተፎካካሪያቸውን እንዳይንቁ ክሊንተን አሳስበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG