የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የሰሜን ኮርያን በመሳሰሉ አጣዳፊ ጉዳዮች ላይ ለማትኮር ሲሉ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በአንድ ቀን ያሳጥራሉ።
የቻድና የናይጀርያ ኦፊሴላዊ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአንድ ቀን ቀድመው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ሲሉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቲቭ ጎልድስተይን ዛሬ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሰሜን ኮርያ መሪ ኪም ዦንግ ኡን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ከሰሜን ኮርያ የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸውን ያስታወቁት ቲለርሰን አፍሪካን ይጎበኙ በነበረበት ወቅት ነው።
ቲለርሰን ዛሬ ከቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ጋር ለመነጋገር ኢንጃሚናን ጎብኝተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ጥቅምት ወር በቻድ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በቅርቡ ልታነሳ እንደምትችል ቲለርሰን ወደ ኋላ ጠቁመዋል።
የቻድ መንግሥት በሚሰጠው ፓስፖርት ላይ ቁጥጥር ለማጠናከር የሚያስችል እርምጃ ወስዷል። የመረጃ ልውውጥ ሥራም አሻሽሏል ብለዋል ቲለርሰን።
ሬክስ ቲለርሰን ወደ ሀገራቸው ከማምራታቸው በፊት ከናይጀርያው ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪ ጋር ለመነጋገር ወደ ናይጀርያ መዲና አቡጃ በአይሮፕላን ሄደዋል።
ቲለርሰን ባለፈው ቅዳሜ አሟቸው ስለነበር በኬንያ አንዳንድ ኩነቶችን ሰርዘዋል። አሁን ግን ደህና ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለ ሰሜን ኮርያና ስለሌችም ነጥቦች በሚከናወኑ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ነገ ዋሺንግተን ይገባሉ ሲሉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቲቭ ጎልድስተይን አሳታውቀዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ