በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወጣቶችን ቀልብ ያሸነፈው ቲክ ቶክ አፕሊኬሽን/መተግበሪያ/


ቲክ ቶክ የተሰኘው አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚሰራጩበት አዲሱ መተግበሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበርካታ ኢትዮጵያንን ቀልብ የሳበ ቴክኖሎጂ ሆኗል። በቻይና የሚገኝ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የፈጠራ ውጤት የሆነው ይህ መተግበሪያ በተለይ በወጣቶችና ህፃናት ዘንድ ፈጣን ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን ከታዋቂ ተዋንያን በተጨማሪ ከዚህ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ ያልነበራቸው ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያጋሩበት እድል እንደፈጠራላቸው ይናገራሉ። ቲክ ቶክ በኢትዮጵያ ውስጥ እያገኘ ያለውን ተቀባይነትና ወጣቶች በምን መልኩ እየተጠቅሙት ነው?

ቲክ ቶክ የተሰኘው መተግበሪያ በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ አራት አመታትን አስቆጠረ። በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዝናኝነቱ በብዙ ወጥቶች ዘንድ ተመራጭ የማህበረሰብ ሚዲያ መሆን የቻለው ቲክ ቶክ እስካሁን ከ 800 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራት ችሏል።

ይህ ወጣቶች የሚያዘወትሩት መተግበሪያ ኢትዮጵያ ውስጥም ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ይገኛል። በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ህፃናትና ልጆች እቤት በዋሉበት ወቅት የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመሩ ይነገራል።

በተንቀሳቃሽ ምስሎቹ ላይ ከሚሰሙት ድምፆች ጋር የአፋቸውን እንቅስቃሴ አመሳስለው በመናገር፣ አስመስለው በመተወንና የዳንስ ስልቶችን በመከትል በቲክ ቶክ በሚለቋቸው ቪዲዮዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀልብ ውስጥ ከገቡ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች መሀል ድግሞ ሀያት ናስር እና የትናየት ታዬ በቅድሚያ ተጠቃሽ ናቸው።

በወሊሶ ተወልዳ ያደገችው የ 23 አመቷ ወጣት ሀያት ናስር ቲክ ቶክን በተቀላቀለች በ ስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ከ 134 ሺህ በላይ ተከታዮችን ማፍራት ችላለች።

በሀዋሳ ዩንቨርስቲ የ ሶስተኛ አመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ሀያት ቤተሰቦቿ በገዙላት ስልክ እንደ ቀልድ መጫን የጀመረቻቸው ቪድዮዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት እንዳገኙላት ትናገራልች።

ከልጅነቷ ጀምሮ ደራሲና የፊልም ዳይሬክተር የመሆን ህልም የነበራት ሀያት ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የትወና ልምድ ሳይኖራት አስመስላ በመጫወት በቲክ ቶክ በምትለቃቸው ቪዲዮዎች ያሳየችው የትወና ብቃት ብዙ አስታየያት ሰጪዎችን አስደምሟል። ሀያት ግን አዳዲስ ክህሎቶችን በቲክቶክ ይዤ የመጣሁት እኔ ብቻ አይደለሁም ስትል በርካታ ወጣቶችና ታዳጊዎች ቲክ ቶክን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ትገልፃለች።

ልክ እንደ ሀያት በቲክ ቶክ ላይ በምትለቃቸው ቪድዮዎች ከ 130 ሺህ በላይ ተከታዮችን በአጭር ጊዜ ያፈራችው ደግሞ ሌላዋ የ23 አመት ወጣት የትናየት ታዬ ናት። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት የአምስተኛ አመት ተመራቂ ተማሪ የሆነችው የትናየት በኮሮና ምክንያት እቤት ውስጥ በመዋሏ፣ ለጊዜ ማሳለፍያ ብላ መስራት የጀመረቻቸው የአንድ ደቂቃ ቪድዮዎች ዛሬ ተፅእኖ ፈጣሪ እንድሆን አድርጎኛል ትላለች።

አሁን ባለንበት ትውልድ፣ የማህበረሰብ ሚዲያዎች መረጃን በቀላሉ ለህዝብ በማድረስ ረገድ ያላቸው ሚና ቁልፍ ሆኖ ሳለ፣ የጥላቻ ንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎች የሚሰራጩበት ዋና መንገድ ሆነውም ጥፋትን አስከትለዋል ። በቲክ ቶክ አዝናኝ የቀልዶችን ከመልቀቅ ባለፈ ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ትምህርቶችን የሚያስተላልፉ ቪዲዮዎችን መስራት የጀመረችው የትናየትም በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታየው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጉድለት ያሳስባታል።

ቲክ ቶክ ላይ በርካታ አድናቂዎችንና ተከታዮችን ከማፍራት ባሻገር የትናየትና ሀያት ገንዘብም እያገኙበት ነው። የተለያዩ መተግበሪያ ባለቤቶችና አምራቾች ወጣቶቹን ማስታወቂያ በማሰራት ይከፍሏቸዋል። የገቢ ምንጭ መሆኑ የበለጠ እንድሰራ ያበረታታኛል የምትለው ሀያት በኮሮና ምክንያት የተዘጋው ትምህርት ቤት ቢከፈት እንኳን ከትምህርቴ ጎን ለጎን እቀጥለዋለሁ ትላለች።

ልክ እንደ ሀያትና የትናየት ያሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች በብዛት እየተጠቀሙት የሚገኘው ቲክ ቶክ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት የደህንነት ስጋት ጥያቄ ይነሳበታል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መተግበሪያው ከአሜሪካውያን ተጠቃሚዎች መረጃ እየሰበሰበ ለቻይና መንግስት ይሰጣል በሚል አግደውት የነበረ ቢሆንም ከቻይናው ኩባንያ ጋር በተደረግ ድርድር የአሜሪካ ኩባንያዎች ድርሻ እንዲኖራቸውና በመረጃ አጠባበቅ ላይ ስምምነት ላይ በመደረሱ ቲክ ቶክ በአሜሪካ ለሚገኙ ከ 80 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጠቃሚዎቹና በዓለም ዙሪያ ላሉ ወጣቶች አገልግሎቱን መስጠት ይቀጥላል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

የወጣቶችን ቀልብ ያሸነፈው ቲክ ቶክ አፕሊኬሽን/መተግበሪያ/
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:41 0:00


XS
SM
MD
LG