በትግራይ ክልል እምባስነይቲ ወረዳ ውስጥ አንድ ባልደረባው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አስታወቀ።
የአምቡላንስ አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ወልዱ አረጋዊ የተባሉ ባልደረባው የተገደሉት በምጥ የተያዘች እናት ወደ ሐኪም ቤት ለመውሰድ በመጓዝ ላይ ሳሉ መሆኑን ማኅበሩ አመልክቷል።
ነበለት ከተባለች ከተማ ‘ዓዲ ጉደም’ የተባለ ቀበሌ የሕክምና ባለሙያ ይዘው ሲጓዙ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ጥይት ተተኩሶባቸው ወደ ህክምና እየተወሰዱ ሳለ ህይወታቸው ማለፉን ቀይ መስቀል አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ እና የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መስፍን ደረጀ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል ሰብዓዊ አገልግሎትን የሚያደናቅፍ በመሆኑ የሚወገዝ አድራጎት ነው ብለዋል፡፡ ተመሳሳይ አድራጎት በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች እየተፈፀመ ነው ያሉት አቶ መስፍን የሰብአዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ችግር ባለበት ቦታ እየገቡ ህዝብ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ደህንነታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የእምባስነይቲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኪዳነማርያም ሱራፌል እርሳቸው በሚያስተዳድሩት አካባቢ ይሄንን መሰል ግድያ በመፈጸሙ ማህበሩን ይቅርታ ጠይቀው ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ፡፡
መድረክ / ፎረም