ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት ማካሄድ የጀመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ውይይቱ አስተዳደሩ ያሉበትን ክፍተቶች ለማረምና አዎንታዊ ነገሮችን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል። አቶ ጌታቸው፣ ትላንት ማክሰኞ፣በዓዲግራት ከተማ በነበረው ውይይት ላይ ባደረጉት ገለጻ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በሚመሩት ሰዎች ላይ "ከፍተኛ የሆነ ስም የማጥፋት ሥራ ተፈጽሟል" ሲሉ ተችተዋል።
በቅርቡ በተካሄደው 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ "እንደ ፓርቲ ስራዎች በሚገመገሙበት ወቅት የግለሰቦች ስም አብሮ ሊነሳ ይችላል እንጂ፤ ስም የማጥፋት ድርጊት የሚባለው ትክክል አይደለም" ብለዋል። በሌላ በኩል ተቃዋሚው ዓረና ፓርቲ በሰጠው መግለጫ፣ በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል ክልሉን ‘ሌላ የጸጥታ ችግር ውስጥ አስገብቶታል’ ሲል ተችቷል ።
በሌላ ዜና በአፍሪካ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፈጻጸም ከተፈራራሚዎቹ ወገኖች ጋር ለመገምገም ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም