የትግራይ ክልል የጸጥታ አመራሮች፣ በእነ ዶ.ር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማስተካከል ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ ዛሬ በአወጡት መግለጫ አስታወቁ።
በእነ ዶ.ር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን ከዚህ ቀደም አደረግኩት ባለው ጉባኤ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 13 ሰዎች ከሥልጣናቸው እንዲነሱ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በተሰጠው ውሳኔም ከስልጣናቸው በተነሱት ሰዎች ምትክ ሌሎች አመራሮች መመደቡን እና ፕሬዝዳንቱን በተመለከተ ግን ውሳኔውን ለፌደራል መንግሥቱ መሰጠቱን ተገልጾ ነበር።
የጸጥታ አመራሮቹ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ 50 ሲደመር አንድ አብላጫ ድምጽ ያለው ጉባኤ በማካሔድ ውሳኔ ላሳለፈው በእነ ዶ.ር ደብረ ጽዮን ለሚመራው ህወሓት ቡድን ድጋፋቸውን እንደሚሰጡና በጉባኤው የቀረበውንም ሐሳብ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ “ውሳኔው ተቀባይነት የሌለው ትልቅ ስህተት ነው” ሲሉ ተቃውመውታል።
አዛዦቹ በመግለጫቸው፣ ከትግራይ ክልል ከመከላከያ ሰራዊት ውጭ ያሉ ሓይሎች ካልወጡ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን ሒደቱን እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
ዛሬ በንባብ በአሰሙት መግለጫቸው፣ “የትግራይ የሰላም እና ደኅንነት ዋስትና ሳይረጋገጥ፣ ሉአላዊ መሬታችን ሳይመለስ፣ በጠላት ስር ያለው ህዝባችን ነፃ ሳይወጣ፣ የተፈናቀሉ ሳይመለሱ የትግራይ ሰራዊት ይበተን እና ሌሎች ሓይሎች ይግቡ የሚል ሓሳቦች እናወግዛለን።" ብለዋል። "በፕሪቶሪያ ሰምምነት መሰረት ትጥቅ መፍታት እና ሰራዊት መበተን (ዲዲአር) የትግራይ ደኅንነት እና የሠራዊታችን ዝግጁነት ግምት ወስጥ ባስገባ መልኩ በመፈፀም የትግራይ ሰለም እና ደህንነት ለመጠበቅ እንሠራለን” ሲል መግለጫው ጠቅሷል።
ወደ 200 የሚኾኑ ከጄነራል እስከ ኮለኔል መዓረግ ያላቸው የጸጥታ አመራሮቹ መቐለ ከተማ ላይ ከጥር 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ስብሰባ ማካሔዳቸውን ጠቅሰው ዛሬ በአወጡት የአቋም መግለጫ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከተሰጣቸው ተልኮ ውጪ፣ የትግራይ ሕዝብ ጥቅሞች ወደ ጎን ትተው ክህደት ፈጽመዋል በሚል ወንጅለዋቸዋል፡፡
መግለጫው አክሎ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው ተልእኮ የትግራይን ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት መመለስ፣ የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው መመለስ፣ የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመር እና ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መኾን ሲገባው ይኽን ማድረግ አልቻለም” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወቅሷል።
የክልሉ የጸጥታ አመራሮች መግለጫ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አመራር “ደካማ ነው” ያለው ሲኾን፣ "በጊዜያዊ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ መሰረት 50+1 ድርሻ ያለው፣ ፕሪቶሪያ ላይ በተካሔደው ተኩስ የማቆም የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ የነበረውና 14ኛ ጉባኤ ያካሄደው ህወሓት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለማስተካከል የወሰነው ውሳኔ ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፋችንን እንገልፃለን” ብሏል።
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ቡድን በወቅቱ በአካሔደው ጉባኤ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ እና የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት፣ የዞን አስተዳደሪዎች፣ እንዲሁም የኤጀንሲዎችና ኮሚሽኖች ሓላፊዎች ህወሓትን ወክለው የተመደቡ ስለ ነበሩ፣ "ከመስከረም 27 ቀን 2017 ጀምሮ ከስልጣን እንዲወርዱ” የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
የጸጥታ አመራሮቹ በመግለጫቸው የጠቀሱት ይህንን ውሳኔ ሲኾን፣ ከዚህ በተጨማሪም “ሰራዊታችን የወከላቸው የካቢኔ አባላት የሥራቸውን አፈፃፀም ገምግሞ እምነት ባጣባቸው አባላቶቹ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ወስነናል” ብለዋል።
በጉዳዩ ዙርያ ለአሜሪካ ድምፅ ምላሽ የሰጡት የጊዝያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳን ጌታቸው ረዳ፣ የተለያዩ ሓሳብ ያላቸው ሰዎች ያቋቋሙት የመመከት ሓይል የሆነው ሰራዊት፣ የአንድ ቡድን መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር ስህተት እና ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
“የሆነ ሰው ወታደር፣ ታጋይ፣ ፖለቲከኛ ይሁን መሀንዲስ የፈለገውን ቡድን የመምረጥ እና የመደገፍ መብት አለው። ለትግራይ ህዝብ ህልውና ከሁሉም አስተሳሰቦች እና ከሁሉም የትግራይ አቅጣጫ የተውጣጣ የህልወና ኃይል በአጋጣሚ ሓለፊነት ስለያዘ የአንድ ቡድን መጠቀሚያ እንዲሆን መወሰን ግን በመሰረቱ ተቀባይነት የለውም ሊኖረውም አይችልም” ብለዋል።
የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ሓላፊ ሌተናንት ጀነራል ፍስሀ ኪዳኑ የትግራይ ክልል የጸጥታ አመራሮች የሰጡትን መግለጫው አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ በሌላ ቀን እንደሚሰጡን ቃል ገብተው፣ ለአሁኑ የዛሬውን መግለጫ ተጠቀሙ ብለውናል፡፡
በቀጣይ ውሳኔውን ወደ ተግባር ለመቀየር ይህን የህልውና እና የመመከት ሓይል ለመጠቀም መሞከር ስህተት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፣ “ጉባኤ ያካሄደውን አካል እደግፋለሁ የሚል ሰው፣ የትግራይ ሕዝብ ህልውና ለመመከት የተቋቋመን ሰራዊት ለዚህ ማስፈፀሚያ ለማዋል ከሞከረ ትልቅ ስህተት ነው። አሁን የተፈፀመውም ስህተት ነው፣ ከዚህ በላይ እንደማይሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
በሌላ ዜና ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዳግም ለመመዝገብ ባወጣው አዋጅ መሰረት ህወሓት የቦርዱ ታዛቢዎች ባሉበት ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲያካሂድ እና ይህ ካልሆነ ግን ቦርዱ በህጉ መሰረት ውሳነ እንደሚሰጥበት አሳውቆ ነበር።
ጉዳዩን አስመልክቶ በትላንትናው እለት ጉባኤ ያካሄደው ህወሓት፣ በቁጥጥር ኮምሽኑ በኩል ባወጣው መግለጫ፣ ህወሓት የፕሪቶርያ ስምምነትን የፈረመ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ጋራ የሚገናኝ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ፓርቲ ነው ብሏል።
የኢትዮጰያ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ሕጋዊ ያልሆነ እና የፕሪቶርያን ሰምምነት የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለትም አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም