በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባድረግ ቤተሰብና የምግባረ ሰናይ ስራዎቹ


በሐሰን ዓብደላ ባድረግ መኖርያ ቤት የተሰጣቸው እናቶች
በሐሰን ዓብደላ ባድረግ መኖርያ ቤት የተሰጣቸው እናቶች

የመኖርያ ቤቶች ችግር በከፋ መልኩ በሚታይባት የመቀሌ ከተማ ውስጥ ለ24 የተቸገሩ እናቶች የተሟሉ ቤቶች አሰርቶ በነፃ የሚያበረክት ሰው ምነኛ የታደለ ነው ይላል ዘጋብያችን ግርማይ ገብሩ ከከተማዋ በላከው ልዩ ዝግጅቱ።

የሐጂ ሓሰን ቤተሰብ በመቀሌ ከተማ የተቸገሩትን በመርዳት ይታወቃሉ። በመቀሌ በተለምዶ ቀበሌ 14 ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ድልድይ አሰርተው የሕብረተሰቡን ችግር መፍታት መቻላቸው ይታወሳል። በተለይም ሃይማኖት ሳይለያዩ ሁሉንም የሰው ልጅ ወገን እንደሚያግዙ ይነገርላቸዋል። ዕቃዎቻቸው ለቤተ ክርስትያን አገልግሎት ያውሱ እንደነበር ሕብረተሰቡ ዛሬም ድረስ ያስታውሳቸዋል።

ልጆቻቸው ደግሞ በመቀሌ ከተማ በመኖርያ ቤት እጦት ምክኒያት በኪራይ ቤት የተማረሩት ደግሞም ጧሪ የሌላቸው እናቶችን ለመርዳት ከአሁን በፊት የሐጂ ሐሰን ባድረግ ልጅ፤ ሐጂ ዓብደላ ባድረግ ለ12 እናቶች የተሟሉ ቤቶች አሰርተው ማስረከባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

ዛሬ ደግሞ የልጅ ልጃቸው ወጣት ሐሰን ዓብደላ ባድረግ በተመሳሳይ ለ12 እናቶች የሚያገለግሉ የተሟሉ ቤቶች አሰርቶ ሰሞኑን አስረክቧል። እያንዳንዱ ቤት የየራሱ ሽንት ቤትና መታጠብያ ክፍል እንዲሁም የውሃና የመብራት ቆጣሪ የተገጠመለት የተሟላ ቤት ነው።

ሐሰን ዓብደላ ሐሰን የወላጆቹን መልካም ተግባር ተከትሎ የተሟሉ ቤቶች ሰርቶ ለድሃ እናቶች ማስረከቡ ከመጠን በላይ መደሰቱን ገልፆ ከመንግሥትና ከሕብረተሰቡ ሞራል ቤተሰቡ እንደሚያስፈልገው ይናገራል።

ሌላው የሐጂ ዓብደላ ልጅ ዓብደልቃድር ዓብደላ በተመሳሳይ 12 የተሟሉ ቤቶች በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል።

ቤቶቻቸውን ከተረከቡት እናቶች ወይዘሮ ስዕዲ ስዒድ በርሀ፣ ወይዘሮ በርሀ መሐመድ እና ወይዘሮ ሳዓዳ ካሕሳይ ሑሴን በቤት ችግር ምክንያት ለረዥም ዓመታት ያህል ተቸግረው እንደነበር በመግለፅ የማይታለፍ የለም እንደምንም እየኖርን ነበርን ይላሉ።

በአሁኑ ሰዓት ያለምንም መሸማቀቅ የሚኖሩበት ለዛውም የተሟሉ ቤቶች በነፃ በማግኘታቸው ከልብ በማመስገን የባድረግ ቤተሰብን "አላህ ጨምሮ ይስጣቸው" ሲሉ መርቀዋል።

የሐሰን ባድረግ አባት ሐጂ ዓብደላ ባድረግ ከዚህም በላይ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ እየጣሩ እንዳሉ በመግለፅ ይኸውም ሴቶች ብቻ የሚገለገሉበት ዘመናዊ ሆስፒታል ለማሰራት ማቀዳቸውንም ይናገራሉ።

የትግራይ ክልል የሴቶች ማሕበር ስራ አስከያጅ ወይዘሮ ዘነበሽ ፍስሃ ቤቶቻቸውን ከተረከቡት እናቶች ጋር ተገናኝተው ቤቶቹን ከጎበኙ በኃላ "የባድረግ ቤተሰብ እየሰራ ላለው የምግባረ ሰናይ ተግባር ትልቅ ክብርና አድናቆት አለን፤ ሌሎች ባለሃብቶችም ይህንን የተቀደሰ ተግባር እንዲከተሉት ጥርያችንን እናስተላልፋል" ብለዋል።

ሙሉ ዝርዝሩን ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

የባድረግ ቤተሰብና የምግባረ ሰናይ ስራዎቹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:59 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG