የፈረንሣይዋ ከተማ ቱሉዝ አቅራቢያ አንድ ሰው ያሽከረክራት የነበረችን መኪና ሆን ብሎ ተማሪዎች ላይ ነድቶ በሦስት ቻይናዊያን ተማሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ቀደም ሲልም የወንጀል ታሪክ የነበረበት እንደሆነ ባለሥልጣናት ቢያረጋግጡም በታዋቂ ፅንፈኞች ዝርዝር ውስጥ ግን እንደሌለ የፈረንሣይ የዜና ማሠራጫ ጣቢያ ቢኤፍኤም ዘግቧል።
የፈረንሣይ የዜና ወኪል - ኤኤፍፒ ባወጣው ዘገባ ግለሰቡ ተሽከርካሪውን ተማሪዎቹ ላይ የነዳው ሆን ብሎ መሆኑንና ከተጎጂዎቹ አንደኛው በከባድ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።
አንድ ሴትና ኁሀለት ወንዶች የሆኑት ተጎጂዎች ዕድሜአቸው በሃያዎቹ ውስጥ የሚገኝ እንደሆነም ተገልጿል።
ፈረንሣይ ቀደም ሲልም በተሽከርካሪ የሚፈፀሙ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች በእሥላማዊ መንግሥት ቡድን የተፈፀሙባት ይሁን እንጂ የዛሬውን አደጋ ስላደረሰው ግለሰብ ማንነትና ዓላማ ባለሥልጣናቱ የተናገሩት ነገር የለም።
ባለፈው ዓመት የአውሮፓ በጋ ወራት ውስጥ በደቡባዊቱ የፈረንሣይ ከተማ ኒስ አንድ ቱኒዝያዊ ይዞት የነበረን ተሽከርካሪ ሰው ላይ ነድቶ ሰማንያ ስድስት መግደሉ ይታወሳል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ