ዋሽንግተን ዲሲ —
ሰሞኑን በሱዳን በተነሳው ህዝባዊ የተቃውሞ አመጽ፣ ካርቱም ውስጥ፣ ሶስት ታዳጊ ህጻናት፣ አንድ የ14 ዓመት ሴት ልጅና ሁለት የ15 እና 17 ዓመት ወንድ ልጆች መገደላቸው ተገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ባወጣው መግለጫ የታዳጊ ህጻናቱ አሟሟት እየተጣራ መሆኑና ሁኔታውም እንዳሳዘነው አመልክቶ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንደሚመኝ ገልጿል፡፡
ዩኒሴፍ በመግለጫው “ተቃውሟቸውን በሰለማዊ መንገድ በሚገልጹት ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይልን መጠቀም ተቀባይነት የሌለው ሲሆን በወጣቶችና በታዳጊዎች ላይም ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል” ብሏል፡፡
“ህጻናት ሁልጊዜም ከየትኛውም የጥቃት ዓይነት መጠበቅ አለባቸው፡፡ የጥቃት ኢላማም ሆነ ለፖለቲካ እርምጃዎች መጠቀሚያ መሳሪያ መሆን አይገባቸውም” ያለው መግለጫው “የሱዳን ህጻናት የወደፊቷን ሰላማዊ የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊ ሱዳንን የማየት ህልማቸውን ማሳከት ይኖርባቸዋል” ብሏል፡፡