የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እየተካሄደ ባለበት ባሁኑ ወቅት ሰላሳ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ግጭቱና ረሃቡን ለማስቆም በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ እና ለጸጥታ ምክር ቤቱ አባል ሀገሮችቋሚ ተወካዮች መላካቸውን ሬፉጂስ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታወቋል።
ሬፉጂስ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት እንደዘገበው የድርጅቶቹ መግለጫ “በትግራይ ክልል ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲቪሎች የርዳታ አቅርቦት እንዲሁም የባንክ እና የመገናኛ አገልግሎቶች ተቋርጠውባቸዋል ፤ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በረሃብ ቸነፈር ሁኒታ ውስጥ ወድቀዋል፥ ሌሎች በርካታ ሰዎች ረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ “ ይላል፡፡
በጦርነቱ ወሲባዊ ጥቃቶች፥ ረሃብን በጦርነት መጠቀም እና በጅምላ ማፈናቀልን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል ሲልም ሬፉጂስ ኢንተርናሽናል አክሏል።
“ወደ አጎራባች ክልሎ አፋርና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ግጭትም ለ400 ሺ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነ ሲሆን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ስጋት ሆኗል፡፡” ሲልም መግለጫው አመልክቷል፡፡
ዛሬ መውጣቱ የተነገረለት ደብዳቤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙትን ዜጎች ለመርዳት የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ዋና ጸሀፊና የጸጥታው ምክር ቤት ሊወስዳቸው ይገባል ያላቸውን ውሳኔዎችም ዘርዝሯቸዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ አንደኛ ሰብአዊ ተኩስ አቁም ጥሪ ተደርጎ ሁሉም ኃይሎች ከትግራይ ክልልና ከአካባቢው ክልሎች እንዲወጡ እንዲደረግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ እርዳታ እገዳውን እንዲያነሳና የእርዳታውንም ጥረት የሚያሰናክሉ የቢሮክራሲ እንቅፋቶችን እንዲያስወግድ፣
ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኖችን በማሳማራት በጦር ወንጀሎችና በሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብትና ዓለም አቀፍ ህጎችን በመጣስ ጥሰቶችን አስመልክቶ የሚቀርቡ ክሶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ እንዲደረግ እና እንዲሁም፣ እንደ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያሉትን ጨምሮ በፖለቲካ ተቃዋሚ ቡድኖች መካከል ብሄራዊ ውይይትን እንዲያበረታታ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የድርጅቶቹን ደብዳቤዎች አስመልከቶ የዓለም ቀፍ ስደተኞች ድርጅት ወይም ሬፊጁስ ኢንተራናሽናል የፕሮግራም እና ፖሊሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃርዲን ላንግ እንዲህ ብለዋል፡፡
“የተባበሩት መንግሥታት አመራር ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ያ ማለት በትግራይ የሚገኙ በመቶሺዎች የሚገኙ ሰዎች መካከል ያለ የሞትና የህይወት ልዩነትን ያመለክታል፡፡ በረሀብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የተባበሩት መንግስታትና የጸጥታው ምክር ቤት ከመርፈዱ በፊት ህይወትን ለማዳን ፈጣንና ቆፈጠን ያለ እምርጃ እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡ የተዘጋጋው ተከፍቶ የሰ አብዊ እርዳታው እጅግ ለሚያስፈልጋቸው እንዲደርስ የግጭቱ ተሳታፊዎች ችግሩን በሚፈትቡት መንገድ ላይ መደራደር ይኖርባቸዋል፡፡”
ደብዳቤው ላይ በፊርማቸው ካኖሩት ድርጅቶች ውስጥ አሊያንስ ፎር ፒስ ቢልዲንግ፣ ብሬድ ፎር ዘወርልድ፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የልማት ድርጅት ኢሲዲሲ (ECDC)፣ ግሎባል ሴንተር ፎር ሪስፖንስብሊቲ ቱ ፕሮቴክት እና የመሳሰሉ ሌሎች የማህበረሰብ፣ የእምነት፣ የመብት ተሟጓች፣ የስደትና ፍልሰት ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡