ከሲድኒ እስከ ሞምባይ፣ ከፓሪስ እስከ ሪዮ ደ ጄኔሮ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች የአውሮፓውያኑን 2025 በአስደናቂ የብርሃን ትዕይቶች፣ በረዶ ውስጥ በመነከር እና በተለያዩ ሥነ ሥርዐቶች ተቀብለውታል።
በኒው ዮርክ የአዲሱን ዓመት መግቢያ የሚያበስረው ትልቁ ኳስ ታይም ስኩዌር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ ላይ ሲወርድ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይወርድ በነበረው ዝናብ ውስጥ ኾነው ተከታትለውታል።
ስድስት ቶን የሚመዝነው ኳስ እና 2ሺሕ 688 የሦስት ማዕዘን ቅርፅ ያላቸው ፈርጦች በታይምስ ስኩዌሩ ላይ ሲወርዱም ጥንዶች ተሳስመዋል፣ የተሰበሰበው ሕዝብም ደስታውን ገልጿል።
አዲሱን ዓመት በቅድሚያ የተቀበሉት በደቡባዊ የፓሲፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት ሲሆኑ፣ ኒውዚላንድ 2025 መግባቱን ያበሰረችው የኒውዮርክ ኳስ ከመውረዱ 18 ሰዓታት አስቀድማ ነው። ከዓለም ቀድማ በዓሉን ለማክበር ዕድል ያገኘችው ኦክላንድ ከተማ ውስጥም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ መሐል ከተማ በመጉረፍ እንዲሁም የርችት ትዕይንቶችን ለማየት እሳተ ገሞራ በሚወጣባቸው የከተማዋ የተቆላለፉ ተራራዎች ላይ በመውጣት አክብረዋል።
በተቃራኒው አሜሪካ ውስጥ የምትገኘው ሳሞዓ፣ ኒው ዚላንድ በዓሉን ካከበረቸ ከ24 ሰዓታት በኋላ አዲስ ዓመት በመቀበል የመጨረሻዋ ሀገር ትሆናለች።
እንደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ሱዳን እና ዩክሬን ባሉ አካባቢዎች የሚካሄደው ጦርነት ግን የ2025ን አቀባበል አቀዝቅዞታል።
የርችት ትዕይንቶች
አክላንድ አንዲሱን ዓመት ከተቀበለች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ በአውስትራሊያዋ ሲድኒ ከተማ የሚገኘው ድልድይ በተለያዩ የርችት ትዕይንቶች ደምቋል። ይህን ትዕይንት ለማየትም ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሲድኒ ወደብ አቅራቢያ ተገኝተው ከእንግሊዛዊው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሮቢ ዊሊያም ጋር በጋራ አዚመዋል።
በላስ ቬጋስ ከ340 ሺሕዎች በላይ ሰዎች ከቁማር ማጫወቻ ስፍራዎች የተነሱ የርችት ትዕይንቶችን ተከታትለዋል። ከትዕይንቱ አቅራቢያ የተዘጋጀ ስፍራም የተለያዩ የሰዓት አቆጣጠሮችን በማሳየት በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች አዲስ ዓመት ሲገባ አብስሯል።
በካሊፎርኒያ፣ ፓሳዲና ከተማ የተካሄደውን ደማቅ የሰልፍ ትዕይንት ለመመልከት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየመንገዱ ላይ ድንኳን ተክለው የተቀመጡ ሲሆን፣ በቴኔሲ ግዛት ናሽቪል ከተማ የተዘጋጀውን የሀገረሰብ ሙዚቃ ድግስ ለመታደምም ደግሞ ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎች ተሰባስበዋል።
በደቡብ ኮርያ ያለፈው እሑድ በተከሰከሰው አውሮፕላን ምክንያት ህይወታቸው ያለፈውን 179 ሰዎች ለማሰብ ብሔራዊ ሐዘን በመታወጁ፣ ለአዲሱ ዓመት የተሰናዱ ዝግጅቶች ተሰርዘዋል።
መድረክ / ፎረም