የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ነገ ሐሙስ ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ ላይ ይጀመራል፡፡
ከ64 በላይ ለሚሆኑ ግጥሚያዎች እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ትኬቶች መሸጣቸው ተነግሯል፡፡
የዓለም አቀፉ የስፖርት አስተዳዳሪ ተቋም ፊፋ የዘንድሮው ውድድር ከቀደሙት የሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያዎች የበለጠ ተመልካች ይኖረዋል ብሏል፡፡
እኤአ በ1991 ውድድሩ ሲጀመር የነበሩት ቡድኖች 12 ብቻ የነበሩ ሲሆን ኒውዚላንድ እና አውስትሬሊያ በጋራ በሚያስተናግዱት በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሠላሳ ሁለት ሀገሮች እንደሚሳተፉ ተመልክቷል፡፡
ለአሸናፊው ቡድን የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት ከወዲሁ ውዝግብ አስነስቷል፡፡ ወንዶቹ የዓለም እግር ኳስ አሸናፊዎች የ440 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሲያገኙ ለሴቶቹ የሚሰጠው ግን 110 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በፊፋ ደረጃ ምደባ አንደኛነቱን የያዘችው ዩናይትድ ስቴትስ በተከታታይ ሦስት ጊዜ ዋንጫ በመውሰድ የመጀመሪያ ለመሆን ተስፋ ሰንቃ ቀርባለች፡፡ በደረጃ ምደባው ጀርመን፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሣይ ይከተሏታል፡፡
መድረክ / ፎረም