ዩናይትድ ስቴትስ በዩኤስኤድ ወይም፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት በኩል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ወደ 313 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ እርዳታ እየሰጠች መሆኑን ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአፋር አማራና ትግራይ ክልሎች እየተካሄድ ያለው ግጭት፣ ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋላጠቸው ሲሆን፣ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ማድረጉንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በትግራይ ብቻ 90 ከመቶ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ እርዳታ የሚሻ ነው ያለው መግለጫው፣ በሦስቱም ክልሎች ወደ 1ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በሚቀጥለው ሰኔ፣ ከፍተኛ ረሀብ ለመሰለ አደጋ፣ ሊጋለጡ መቻላቸውን አመልክቷል፡፡
ዛሬ ይፋ የተደረገው አዲሱ እርዳታ፣ ወደ 7 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች፣ አስቸኳይና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን የማህበረሰባዊ ጤና ተቋማትን ለማጠናከር የሚውል መሆኑም ተነገሯል፡፡