በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ዓመታዊ የጽኑ ሴቶች ሽልማት ዛሬ በዋይት ሃውስ ታካሂዳለች


የኩባ ተቃዋሚ እና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ማርታ ቢያትሪስ ሮክ የ"ፅኑ ሴቶች" ተሸላሚ
የኩባ ተቃዋሚ እና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ማርታ ቢያትሪስ ሮክ የ"ፅኑ ሴቶች" ተሸላሚ

ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ አደጋን፣ ፍርሃትንና አስጨናቂ ሁኔታዎችን በቆራጥነት ተቋቁመው ሞያዊ ግዴታቸውን ለሚወጡ ሴቶች የምትሰጠው የ"ፅኑ ሴቶች" ሽልማት፣ ዛሬ ምሽት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን እና የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን በተገኙበት በዋይት ሃውስ ይካሄዳል።

የዘንድሮው ሽልማት የሚሰጠው ከኡጋንዳ፣ ጋምቢያ፣ ሞሮኮ፣ አፍጋኒስታን፣ ባንግላዲሽ፣ ቤላሩስ፣ ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና፣ ሚየንማር፣ ኩባ፣ ኢኳዶር፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ እና ኒካራጓ የመጡ 13 ሴቶች ነው።

ሽልማቱን አስመልክቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ እ.አ.አ በ2007 መሰጠት የጀመረው ሽልማት ዘንድሮም ለሰላም፣ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብት እና የፆታ እኩልነት መከበር በልዩ አመራር ብቃት ለታገሉ ሴቶች እውቅና ይሰጣል።

በዚህ አመት ተሸላሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል ከኒኳራጉዋ የሚሸለሙት ዘጠኝ ሴቶች ባለፈው አመት ከእስር የተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች ሲሆኑ "በአፋኝ አገዛዝ ስር ለዲሞክራሲ እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ትግል መቀጠላቸውን" የውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።

ዩጋንዳይቷ አጋተር አቱሃይሬ በዩጋንዳ ሰብአዊ መብት እና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እየሠራች ባለችው ሥራ የምትሸለም ሲሆን የባንግላዲሿ ፋውዚያ ካሪም ፊሮዝ ደግሞ በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድቤት ለተገለሉ ቡድኖች በመታገል በሠራችው ሥራ ክብር ተሰጥቷታል።

ከቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና የምትሸለመው አዥና ጁሲክ በበኩሏ በጦርነት ጊዜ በተፈፀመ አስገድዶ መድፈር የተወለዱ ሕፃናትን ወክላ በሰራችው ስራ እውቅና ተሰጥቷታል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የ'ፅኑ ሴቶች' ሽልማት ኢትዮጵያዊቷ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ፣ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለደረሱባቸው ሰዎች ድጋፍ በማድረግ እና ጥቃት አድራሾች ተጠያቂ እንዲኾኑ ድምፅዋን በማሰማት በአሳያችው ብቃት ተሸላሚ ኾና ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG