በዩናይትድ ስቴትስ ቤተሰቦችና ጓደኞች ከያሉበት ተጉዘው አብረው በሚያሳልፉት የዛሬው የምስጋና ቀን (ታንክስጊቪንግ ዴይ) በዓል ኮሮናቫይረስ ይበልጡን ይዛመታል የሚል ስጋት ፈጥሯል። በርካታ ክፍለ ግዛቶች ባለሥልጣናት የኮሮናቫይረስ መዛመትን ለመግታት አዳዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃዎችን እየወሰዱ ናቸው።
ይሁንና የኒው ዮርክ አስተዳደር የቫይረሱ መዛመት በበረታባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ቤተ ዕምነቶች መገኘት የሚችሉ ምዕመናን ቁጥር ላይ ያወጣውን ገደብ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጊዜያዊ እግድ ጥሎበታል።
ሃገረ ገዥ አንድሩው ኮሞ ያወጡትን ገደብ በመቃወም የኒው ዮርክ ብሩክሊን ቀበሌ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሁለት የወግ አጥባቂ አይሁድ ቤተ እምነቶች ያስገቡትን አቤቱታ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች አምስት ለአራት በሆነ የድምጽ ብልጫ ደግፈውታል።
የቤተ ዕምነቶቹን ቅዋሜ ደግፈው ድምጽ የሰጡት ዳኞች የኒው ዮርክ አስተዳደር በዚያው መመሪያው የምግብ ሸቀጥ እና ሊላም አስፈላጊ ዕቃ ንግድ ቤቶች የፈለጉትን ያህል ደንበኛ እንዲያስተናግዱ ፈቅዶ ሲያበቃ ቤተ ዕምነቶቹን በአስር እስከ ሃያ አምስት ምዕመናን እንዲወሰኑ ማዘዙ አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም ብለዋል።
ከወግ አጥባቂ ዳኞቹ ጋር ድምጽ ያልሰጡት ብቸኛው ወግ አጥባቂ ዳኛ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ ጃን ሮበርትስ ናቸው።
ዳኛ ሮበርትስ የህዝብ ጤና ጥበቃ ባለስልጣናት ለህዝብ ጤና ይበጃል ያሉትን ርምጃ መከልከል ከባድ ነው ብለዋል።