ባለፈው ቅድሜ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ ቁጥሩ ወደ ሶስት መቶ የሚጠጋ ሰው ያለቀበትና ከአራት መቶ በላይ ያቆሰለውን ግዙፍ ፍንዳታ ያደረሱትን በማውገዝ በብዙ ሺዎች የተቆጠረ ሕዝብ ሞቃዲሾና ሌሎችም ከተሞች ውስጥ ሰልፍ አካሄደ።
ትናንት ረቡዕ የተቃውሞ ሰልፉ የተካሄደው ሕዝቡ በብዛት ወጥቶ ለጥቃቱ ሰለባዎች ፀሎት እንዲያደርስ የሞቃዲሾ ከንቲባ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ነው።
የሶማሊያ መንግሥት መኪና ላይ በተጫነ ቦምብ ፍንዳታውን ያደረሰው ፅንፈኛ እስላማዊው ቡድን አልሸባብን ተጠያቂ አድርጓል።
የትናንቱ ሰልፍ ከመካሄዱ አስቀድሞ ራሳቸው ላይ ቀይ የጠመጠሙ ወጣት ወንዶች በከተሞቹ እየተዘዋወሩ ንግድ ቤቶችን በግድ አስዘግተዋል።
“ጠላቶቻንን ይውደሙ፣ አልሸባብ ይውደም” የሚሉ መፈክሮችን ስያሰሙ የነበሩት ሰልፈኞች ሞቃዲሾ ባናዲር ኳስ ሜዳ ሲሰባሰቡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እና ሊሎችም ተቀላቅለዋቸዋል።
ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብዱላሂ መሃመድ ህዝቡ ከአልሸባብ ጋር በሚካሄደው ከባድ ጦርነት ብረት አንስቶ እንዲዋጋ ጥሪ አቅርበዋል።
“አሁን በአንድነት መቆም ይኖርብናል፣ ሁሉም ሶማሊያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ ይህን የጋራ ጠላት መውጋት አለበት” ብለዋል።
ለፖለቲካ መሪዎችም ተመሳሳይ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚደንቱ
“ከውጭ ሀገሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ፖለቲከኞች ልዩነታችንን አስወግደን አብረን ነውጠኞችን እንድንወጋ ጥሪ እስተላልፋለሁ” ብለዋል፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ