በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጦርነትን በመሸሽ መቶ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከሶማሊላንድ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ


በሶማሊላንድ ያለውን ግጭት በመሸሽ 100 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በድርቅ ወደተመታው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መግባታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ኢትዮጵያዊ የስደተኛ ድርጅቶች አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በደቡብ ምሥራቅ ጠርዝ ላይ ከአዲስ አበባ 1ሺህ 300 ኪ.ሜ. ላይ በምትገኘው ዶሎ ያሉ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ የገለጸው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽነር፣ 98 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ድንበር ተሻግረው መግባታቸውን አስታውቋል፡፡

የስደተኞችና የተመላሾች አገልግሎት የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ድርጅት በበኩሉ ሰዎቹን በመመዝገብ ላይ መሆኑንና የተጠቀሰውን ቁጥር ያህል ሰዎች ግብተዋል መባሉን እንደሚስማማ አስታውቋል፡፡

አካባቢው የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሌሉትና በድርቅ የተመታ ቢሆንም፣ ጦርነትን ሸሽተው የመጡትን ሰዎች ግን ተቀብሎ ማስተናገዱን ኃላፊው ተስፋሁን ጎበዜ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡

የረድኤት ድርጅቶቹ ከመድረሳቸው በፊት የአካባቢው ሰው ተቀብሎ እንዳስተናገዳቸው ሃላፊው ጨምረው መናገራቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ዳያን ባልድ በበኩላቸው እስከ አሁን 29 ሺህ ስደተኞች መመዝገባቸውንንና ቁጥሩ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መጠለያ፣ ምግብ፣ ውሃ እና የሕክምና ድጋፍ እንደሚሹ ተወካዩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG