በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ኔታንያሁ ኢራንን ለማጥቃት ከመነሳታቸው በፊት ከገቡበት ማጥ ማውጣት አለባቸው” ኢራን


ፎቶ ፋይል፦ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናሰር ካናኒ
ፎቶ ፋይል፦ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናሰር ካናኒ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ኢራንን ለማጥቃት ከማሰባቸው በፊት፣ "ከገቡበት ማጥ ውስጥ ራሳቸውን በሚያወጡበት ሁኔታ ላይ ማተኮር አለባቸው” ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ ተናገሩ፡፡

ቃል አቀባዩ ናሰር ካናኒ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፣ "በስልጣን ላይ ያለው የጽዮናውያን አገዛዝ በተለይም ወንጀለኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በክልሉ ያሉ ሌሎች የኃይል ማዕከላትን የማጥቃት ከንቱ ምኞታቸውን ትተው ከገቡበት ማጥ ውስጥ ራሳቸውንን ቢያወጡ ይሻላል" ብለዋል፡፡

ይህ የካኒን አስተያየት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት "ኢራንን አናጠቃም ያለው ማነው? እያጠቃን ነው" በማለት የተናገሩትን ተከትሎ የተሰጠ አስተያየት መሆኑን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ኢራን እና እስራኤል ለዓመታት በጦርነት ጥላ ውስጥ ሲጎናተሉ ቆይተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል በሶሪያ ዋና ከተማ በፈጸመችው ጥቃት፣ የኢራን ልዩ ጦር እና አብዮታዊ ዘብ የሚገለገልበት ህንፃ ሲወድም፣ በትንሹ አምስት ኢራናውያን መሞታቸውን የሶሪያ እና የኢራን መንግስት ዜናው አውታሮች ዘግበዋል።

ጥቃቱ የደረሰው እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት ማስፋቷን ተከትሎ በቀጠናው ውጥረት እየተዛመተ ባለበት ወቅት መሆኑ ተመልክቷል።

የእስራኤል ጥቃት በቅርብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ እልቂት ያስከተለና እጅግ አውዳሚ ከሆኑ ወታደራዊ ዘመቻዎች አንዱ ነው ተብሏል፡፡

የጋዛ የጤና ባለስልጣናት እንደሚሉት፣ የእስራኤል ጥቃት ወደ 25,000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ገድሏል፡፡ ሰፊ ውድመት ያስከተለ እና 2.3 ሚሊዮን ከሚሆነው የግዛቱ ህዝብ ከ 80 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ከመኖሪያ ቤታቸው ነቅሏል።

እስራኤል ጥቃቱን የጀመረችው ሐማስ እኤአ ጥቅምት 7 ቀን 1200 ሰዎችን የገደለበትን፣ 250 የሚያህሉትን አግቶ የወሰደበትን እና በእስራኤል ታይቶ የማያውቅ ድንበር ዘለል ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።

አሁን ድረስ ወደ 130 የሚጠጉ ታጋቾች በሐማስ ምርኮ ስር እንደሚገኙ እስራኤል ታምናለች፡፡

ጦርነቱ በቀጠናው ሌላ ውጥረት የቀሰቀሰ ሲሆን ሌሎች ግጭቶችንም ሊያቀጣጠል ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን አሶሴይትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG