በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አጫሽነት ዋናው የሕዝብ ጤና ችግር


የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ጠቅላይ ኃላፊ፤ ሰርጅን ጀነራል ሬጂና ቤንጃሚን
የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ጠቅላይ ኃላፊ፤ ሰርጅን ጀነራል ሬጂና ቤንጃሚን

በሲጋራ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በወር ከሃምሣ ሺህ በላይ ሰው ይሞታል፡፡

የወጣቶች አጫሽነት እጅግ አሣሣቢ እየሆነ መምጣቱንና በአካባቢያችን፣ በጤናችንና በሃገሮች ልማት ላይ ያለውም ጫና ከፍተኛ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ጠቅላይ ኃላፊ፤ ሰርጅን ጀነራል ሬጂና ቤንጃሚን አሣስበዋል፡፡

ዶ/ር ቤንጃሚን አንድ አስደንጋጭ ያሉትን መረጃ ለዓለም አሣውቀዋል፡፡

ባለፉት 18 ዓመታት ሲወጣ የመጀመሪያ የሆነውን የወጣት አጫሽነት አዝማሚያና አካሄድ የሚመለከተውን የመሥሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ከቪኦኤ ጋር በስልክ ቃለ-ምልልስ ያካሄዱት ሬጅና ቤንጃሚን ሪፖርታቸው በወጣቶች መካከል እየተዛመተ ያለውን የማጨስ ወረርሽኝ እንዋጋ ዘንድ ከፊታችን ፈተና ያስቀምጥልናል ብለዋል፡፡

በየዕለቱ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ አሜሪካዊያን በሲጋራ ጠንቅ ምክንያት እንደሚሞቱ የተናገሩት ዶ/ር ቤንጃሚን በሚሞቱት በእያንዳንዳቸው እግር ሁለት አዳዲስ ወጣት አጫሾች እንደሚተኩና ከእነዚህ ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ማጤስ የሚጀምሩት ከ18 ዓመታቸው በፊት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሦስት ሚሊየን የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑ ጨቅላ ወጣቶች ሲጋራ እንደሚያጤሱ ዶ/ር ሬጂና ጠቁመው ዕድሜአቸው ከ18 እስከ 26 ዓመት የሆነ ወጣቶች መካከል አንድ ሦስተኛው አጫሽ በመሆኑ አጫሽነት ዋና የሚባል የሕዝብ ጤና ችግር መሆኙን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሬጅና ቤንጃሚን 18ኛዋ የዩናይትድ ስቴትስ ሰርጂን ጄነራል ናቸው፡፡

ለተጨማሪና ዝርዝር መረጃ ዶ/ር ቤንጃሚንን ያነጋገረውን የሰሎሞን አባተን ዘገባ ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG