በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ሁሉም ሰው ‘ኢትዮጵያ’ ሲል ማየት ደስ ይላል” - ቴዲ አፍሮ


ቴዲ ዋሽንግተን ዲሲ የሙዚቃ ኮንሰርት በነበረው ጊዜ። ፎቶ፡ ሱራፌል ሽፈራው
ቴዲ ዋሽንግተን ዲሲ የሙዚቃ ኮንሰርት በነበረው ጊዜ። ፎቶ፡ ሱራፌል ሽፈራው

ከሙዚቃ ሥራዎቹ በተጨማሪ በኢትዮጵያዊ ማንነት፣ በአንድነትና በፍቅር ዙሪያ አተኩሮ ስለሚሠራ በርካቶች ከዘፋኝነት በላይ አልቀው ይመለከቱታል። ቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን አዲሱን አልበሙን በተመለከተ ከጽዮን ግርማ ጋር ቆይታ አድርጓል።

“ሁሉም ሰው ‘ኢትዮጵያ’ ሲል ማየት ደስ ይላል” - ቴዲ አፍሮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:28:43 0:00

“ጥቁር ሰው” የተሰኘው አራተኛ አልበሙን ካወጣ ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ በቅርቡ ይዞት የመጣው አልበም በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ በዓለም ሙዚቃ ዘርፍ በቁንጮነት ተቀምጧል፡፡ በመጀመሪያው የአልበሙ ሕትመት 600 ሺሕ ቅጂ በማሳተም በሀገሪቱ የሙዚቃ ኢንደስትሪም ሪከርድ ሰብሯል።

በኢንተርኔት አልበሞችን በሚሸጡ ድረ ገጾችም በከፍተኛ ቁጥር ከተገዙት ተርታ ተመድቧል፡፡ ይፋዊ የዩቲዩብ ገጹ ላይ የጫነው ነጠላ ዜማው ተመልካች ብቻ አራት ሚሊዩን ተሻግሯል።

ቴዲ ይህንን “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን የሙዚቃ አልበም ከማውጣቱ ዋዜማ ጀምሮ የነበረውን የአድናቂዎቹን ጉጉት እንዲሁም በርካቶች ከዘፋኝነት አልቀው እንደሚመለከቱት ለተጠየቀው ፤ “የተደከመበት ነገር ውጤት አምጥቶ፣ የምትፈልጊው መልዕክት ሰዎች ጋር ደርሶ፣ የሚፈጥረውን ነገር እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም። ይሕ የእግዚያብሔር ፀጋ ነው በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም ላመሰግን እወዳለሁ” ሲል ምላሹን በምስጋና ጀምሯል።

ቴዲ በአድናቂዎቹ በጣም መጠበቅ በኪነጥበብ እና በፈጠራ ሥራ ላይ እንደሚጠመድ ሰው ጫናን አያሳድርብህም ወይ? ነፃነትንስ ይሰጥሃል? በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ደግሞ፤

“የሰውን የፍቅር መጠን ማየት በራሱ ያስፈራል”

“እውነቱን ለመናገር የሰውን የፍቅር መጠን ማየት በራሱ ያስፈራል። እንደዚህ መወደድ ያስፈራል። ይህን መወደድ የሚሰጥ እግዚያብሔር ነው። እኔ ይህንን ነው የማውቀው። ሁሉን ነገር የሚያደርገው እርሱ ነው። እግዚያብሔር ኢትዮጵያን አይተዋትም። ይሄ የትውልዱ የጋራ ድምጽ ነው። እኔም ደግሞ የትውልዱ አካል እንደመሆኔ የሁላችንም ድምጽ፣ አብረን አምጠን ያመጣነው ነገር ነው።” ካለ በኋላ “የጋራ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነገር ነው ። አብረን የምናዜመው እና ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ ላይ ነው እንግዲህ እንደ ዕድል ኾኖ የደረሰን ለኛ…. እና እዚህ ጊዜ ላይ ሁላችንም ተባብረን ኢትዮጵያ የምንልበት ዕድል እግዚያብሔር ከፍቶልናል ብዬ አስባለሁ። በእውነት ለመናገር የሰው ምላሽ እኔ በሰጠኋቸው መጠን ነው ብዬ አላምንም። እዚህ ላይ የሚታየው አንድ ሰው ለሐገሩ ያለው ፍቅር፣ ለኢትዮጵያዊነት ያለው ፍቅርና በጋራ ለኖረው ነገር ያለው እምነት ነው። ይህን ስሜት የፈጠረው” ብሏል።

ቴዲ የአድናቂዎቹና የሙዚቃ አድማጩ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ለመነቃቃቱ ዋነኛ ምክንያት ከሀገር ፍቅር የመነጨ እንደሆነ ገልፆታል እንደ ቴዲ አፍሮ በጉልህ ስለመወደዱ ለተጠየቀው ግን “እንደ ቴዲ ላልሽኝ በእውነት እኔንጃ የምለው ነገር የለኝም ከባድ ነው………ከባድ ነው…… ” ሲል በረጅም ትንፋሽ ጨርሶታል።

ቴዲ “ኢትዮጵያ” በተሰኘው አልበሙ አተኩሮ የሰበከው አንድነትና ለኢትዮጵያዊ ማንነት በጋራ መቆምን ነው። “የሀገር ሕልውና የራስ ህልውና ነው። ሀገራችን መዳን የምትችለው ኢትዮጵያዊ እንደቀደመው መንፈስ በአንድነት ኾነን በፍፁም ቅንነት ለመቀጠልና ለማስቀጠል በጋራ ስንጥር ነው። ምክንያቱም ይሄ ቢሆን ደስ ይለኛል የሚባል አይደለም። መሆን ያለበትና የሕልውናችን መሰረት ነው።” ብሏል።

“ምልክት የሌለው ሕዝብ ይጠፋል፤ ራዕይ የሌለውም ሕዝብ ይጠፋል”

ከሐሳብ ፍጭትና በጋራ ጉዳይ ላይ ከመመካከር ይልቅ ብዙሐኑንም ባይወክል በተወሰነ መልኩ በቋንቋና በጎሳ ያለ ማተኮር እንዳለ ጠቁሞ “ይህን ደግሞ በተቻለ ሁኔታ አስተካክለን ወደ ጋራ ጉዟችን ለመሄድ መጣር አለብን ብሏል።” ቴዲ የረሃብን ጉዳይም በመቆጨት መንፈስ አንስቷል “ብዙ መብላት ያለባቸው ሰዎች አሉ፣ ብዙ የተራቡ ሰዎች አሉ ታሪካችን በረሃብ ተበላሽቷል በዚህ እራሱ መቆጨትና መናደድ አለበን። ቁጭት ከሌለም ወደ ለውጥ ለመሄድ ሃይል አናገኝም” ሲል ኢትዮጵያውያን ስሜታቸውን ዋጥ አድርገው ረሃብንም ጭምር ለማጥፋት መተባበር እንዳለባቸ መክሯል።

“እኛ ሰላምና ፍቅር አንድነት እንፈልጋለን ኢትዮጵያ ዋስትናችን ናት። ሕልውናችን ነው እና ለዚህ ሕልውናችን የጋራ ስሜታችን የተገለጠበት አጋጣሚ ነው።” ያለው ቴዲ “ብዙ የሚያግባቡን አብረን ያደረግናቸው ጥሩ ነገሮች አሉ ወደ ላይ ነው መሄድ ያለብን ወደ ትንሹ መስመር ከተሰበሰብን አስቸጋሪ ነው።” ብሏል።

ዘፈኖቹ ለፖለቲካዊ ትርጉም ክፍት መሆናቸውን …. የሠራውስ አስቦበት እደሆነ ተጠይቆ ፤ “እያንዳንዱ ዘፈኖች….የጋራ…. ሕይወታችንን አንድነታችንን አብረን የኾናቸውን አብረን ያዘንባቸውን አብረን የተደሰትንባቸውን ብዙ አብረን ያደረግናቸውን ነገሮች እንዲገልጹ አድርጌ አስቤበት ነው የሠራሁት” ብሏል።

ቴዲ በነገስታት ላይ ለምን ትኩረት ታደርጋለህ? ተብሎ ሲጠየቅ “ምልክት የሌለው ሕዝብ ይጠፋል። ራዕይ የሌለውም ሕዝብ ይጠፋል ለዚህ ነው እዚህ የደረስነው ። ስለዚህ እንዲህ የጎሉ ምልክቶቻችንን ደግሞ ከነተግባራቸው ከነሥራቸው ሊወደሱና ሊጋቡብን ይገባል።” ብሏል።

አድናቂዎቹ ለሰጡት ምላሽ “በእውነት ለመናገር የሰዉ ምላሽ እኔ በሰጠኋቸው መጠን ነው ብዬ አላምንም። እዚህ ላይ የሚታየው አንድ ሰው ለሐገሩ ያለው ፍቅር፣ ለኢትዮጵያዊነት ያለው ፍቅርና በጋራ ለኖረው ነገር ያለው እምነት ነው። ይህን ስሜት የፈጠረው” ብሏል።

ሙሉውን ከቃለ ምልልሱን አድምጡት።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG