የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሳን በሃገሪቱ የህዝብ ሀብት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ፣ የሃገራቸው ሴቶች ብዙ ልጅ እንዳይወልዱ እና የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ ሲሉ አሳሰቡ።
የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው በምሥራቅ አፍሪካ ታንዛኒያ ከሶማሊያ፣ ኮንጎ እና ቡሩንዲ ቀጥላ በወሊድ ቁጥር ከፍተኛ አሃዝ የምታስመዘግብ ሃገር ነች።
የፕሬዚዳንት ሃሳን አቋም ዛሬ በህይወት ከሌሉት የቀድሞ ፕሬዝደንት ጃን ማጉፉሊ በተቃራኒው የሚታይ ነው።
ማጉፉሊ ሴቶች ወሊድ መቆጣጠሪያን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ያበረታቱ ነበር።
የአሜሪካ ድምጹ ቻርለስ ኮምቤ ከዳር ኤስ ሰላም በላከው ዘገባ ፕሬዝደንቷ ይህን ያሉት በሃገሪቱ ምዕራብ ክልል ለተሰበሰቡ ነዋሪዎች ንግግር ባሰሙበት ወቅት ነው። የፓርቲያቸው የሕዝብ ግንኙነት መሪና የርዕዮተ-ዓለም ጉዳይ ፀሃፊ “አስፈላጊ የሆኑት በቂ አቅርቦቶች ስላሉ ሴቶች ተጨማሪ ልጆችን እንዲወልዱ” ሲሉ ማበረታታቸውን ተከትሎ የመጣ አስተያየት ነውም ተብሏል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህዝብ እና የስነ ተዋልዶ ፕሮግራም /WFPA/ የተገኘው አሃዝ እንደሚያመለክተው የታንዛኒያ ህዝብ ቁጥር በዓመት በ2.7 በመቶ አካባቢ በማደግ ላይ ሲሆን፤ ብዙ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች የተጨናነቁ ናቸው። በርካታ ወጣቶችም ሥራ-አጥ መሆናቸው ይታወቃል።
ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም ባንክ የተሠራ ጥናት እንደጠቆመው፣ በታንዛኒያ አንዲት ሴት በአማካይ አምስት ልጆች ስትወልድ፣ ይህም በልጅነት በመዳርና የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር ዝቅተኛ በመሆናቸው ነው ተብሏል።
ታንዛኒያ 60 ሚሊዮን ህዝብ ሲኖራት፣ አማካይ የወሊድ መጠኑም በዓለም ካሉት ከፍተኛው ነው።