የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በታንዛኒያ ዛንዚባር ደሴት ላይ የሚያደርጉት ውይይት እንደቀጠለ ነው፡፡ ድርድሩ፥ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ሁከት እና አለመረጋጋት የማስቆም ተስፋ ተጥሎበታል።
በኬንያ እና በኖርዌይ አደራዳሪነት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል፣ ውይይቱ ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በጎሣ ግጭት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ውጥረት እያየለ በመጣበት ወሳኝ ወቅት ነው።
የሰላም ድርድሩ፣ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቀጠለውን ግጭት እና አለመረጋጋት እንደሚያስቆም ተስፋ የሚያደርጉ ብዙዎች፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ውይይት በአዎንታ ተቀብለውታል።
በታንዛንያ የውጭ ግንኙነት ማዕከል መምህር እንደኾኑት አባስ ሙዋሊሙ ያሉ ተንታኞች፣ ኹኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ነው። የቅድመ ድርድር ንግግር መጀመሩ፣ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚወስድ ርምጃ ነው፤ ያሉት ግጭቶቹን ሲከታተሉ የቆዩት ሙዋሊሙ፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የበለጠ መሠራት እንዳለበት ያሠምሩበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ለሰላም ንግግር መቀመጣቸው፣ ግጭቱ እያሳደረ ያለውን ጫና መረዳታቸውን እንደሚያሳይና አሁን በጋራ ችግሩን ለመፍታት ማሰባቸውን እንደኾነ መምህሩ አስረድተዋል፡፡ ንግግራቸው ስኬታማ የመኾን ዕድል እንዳለው ጠቁመው፣ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን ለመከለስና ኢትዮጵያን አንድ በሚያደርግ መልኩ ለማየት ቢመርጡ የበለጠ ስኬት ሊመጣ እንደሚችል መክረዋል፡፡
እንደ ሙዋሊሙ አስተያየት፣ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ ክልሎች የራሳቸው አስተዳደር እንዲኖራቸው መፍቀዱ፣ ሕዝቦች የመገንጠል ፍላጎት እንዲኖራቸው ያበረታታል።
በቀጣናው ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን የሚከታተሉት ሌላው ተንታኝ፣ ኢብራሂም ራሂብ በበኩላቸው፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ብሔራዊው የጸጥታ ተቋማት ለማካተት በሚደረገው ጥረት፣ እያየለ የመጣው ውጥረት የሚያሳየው፣ ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሒደቱን በጥንቃቄ ማስኬድ እንዳለበት ነው፤ ይላሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ብሔራዊ የጸጥታ ተቋማቱ ለማካተት ያሳለፈው ውሳኔ ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩን ኢብራሂም ያወሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኹሉም ክልሎች፣ የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚያስተዳድሩ በመኾኑ፣ መንግሥት ከሁሉም ክልሎች የጦር መሣሪያዎችን በአንድ ጊዜ ማንሣት የሚችልበትን መንገድ መፈለግ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ፡፡
በዛንዚባር ደሴት ላይ እየተካሔደ ስላለው ድርድር አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የመንግሥቱ ዋና ቃል አቀባይ ቻርለስ ሂላሪ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የሚደረገው ንግግር፣ በዝግ እየተካሔደ በመኾኑ፣ ስለ ውይይቱ ምንም ዐይነት መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ዛንዚባር ለውይይቱ የሚኾን ቦታ ከማዘጋጀት ውጪ፣ የድርድሩ አካል አለመኾኗንም ጨምረው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት ጋራ ለመደራደር የሚያደርገው ጥረት የተለያዩ ምላሾችን እያስተናገደ ነው። አንዳንዶች፣ ንግግሩ ግጭቱን ለመፍታት የሚያስችል አንድ ርምጃ ነው፤ ብለው ያበረታታሉ፡፡ እንደ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ያሉ ሌሎች አካላት ደግሞ፣ ትርጉም ያለው ድርድር ከመካሔዱ በፊት፣ “ሸኔ” በማለት የሚጠሩት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚያደርሰው ጥቃት ስለ መቆሙ መረጋገጥ አለበት፤ ይላሉ።
የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ረቡዕ ዕለት በአወጣው መግለጫ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች፣ በእነዚህ ኃይሎች ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ይችላል፤ የሚለው ስጋት መቀረፍ ይኖርበታል፡፡ አልያ ትርጉም ያለው ድርድር ሊካሔድ አይችልም፤” ብሏል፡፡ በተደጋጋሚ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል እየፈጸሙ እና በንጹሐን ሰላማዊ ዜጎች ላይ
እልቂት እያደረሱ ያሉት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት - ሸኔ የሚፈጽማቸው ጥቃቶች መቆማቸውን ማረጋገጥ ዋና ነገር እንደኾነም፣ ኮሚቴው አመልክቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በቁጥር እያደገ መጥቷል፤ የኦሮሚያ ክልልም፣ ከፍተኛ ብሔር ተኮር ጥቃት እያስተናገደ ነው። መንግሥት ለነዚኽ ጥቃቶች፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ ቢያደርግም፣ ቡድኑ ግን አይቀበለውም። ግጭቱን ለማስቆም፣ መንግሥት በአጸፌታ የሚወስደው ርምጃም፣ ከባድ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ምሬት እንዲፈጠር አድርጓል።
ይህም ኾኖ ታጣቂው ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ስጋት ለመፍጠር፣ አደረጃጀት እና የጦር መሣሪያ እጥረት እንዳለበት፣ አንዳንድ ባለሞያዎች አስተያየት ይሰጣሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ውይይት፣ ለተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ሲኾን፣ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።
/ቻርለስ ኮምቤ ከዳሬሰላም ያደረሰንን ዘገባ፣ ስመኝሽ የቆየ ወደ ዐማርኛ መልሳዋለች/